ሚያዚያ 08 ቀን 2017 (መናኸሪያ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ በቡና ምርቷ የምትታወቅ ሲሆን አሁን ላይ የሀገር ዉስጥ የቡና ፍላጎት መጠን በመጨመሩ ወደ ውጪ የሚላከዉ ምርት እየቀነሰ ነዉ ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ከቡና ምርት ከፍተኛ ገቢ ለማግኘት በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት ባለፈው 9 ወራት ወደ 300ሺ ቶን የሚጠጋ ቡና ለውጭ ገበያ በመላክ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡
በቀጣይ 3 ወራት 500 ሚሊየን ዶላር ገቢ በማግኘት ዓመታዊ ገቢውን 2 ቢሊየን ዶላር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ገልጸዋል።
የሀገር ውስጥ ፍላጎት መጨመር፤ የህገ-ወጥ ንግድ መበራከት፤ የሎጂስቲክ እና መሰረተ ልማት እጥረት ብሎም በየጊዜው የአለም የቡና ዋጋ ተለዋዋጭ መሆን የዘርፉ ተግዳሮት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ዳይሬክተሩ የአለም የቡና ዋጋ ሲጨምር ላኪዎች ተጠቃሚ ስለሚሆኑ ምርቱን በብዛት የማቅረብ ነገር ይስተዋላል ብለዋል፡፡ በተቃራኒው የመግዛት ፍላጎት እና የዋጋ መቀነስ ሲስተዋል ደግሞ ለአገር ውስጥ ገበያ የማቅረብ ሁኔታ እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡
እንደዚህ ዓይነት ተግባራትን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን የቁጥጥር ስራ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን የቡና ምርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢሆንም ተጠቃሚውም በዛው ልክ በመጨመሩ ምርት እና ምርታማነት እና አምራች አርሶ አደሮችን ማበራከት ላይ በአጽኖት ለመስራት በእቅድ መያዙን ገልጸዋል።
ምላሽ ይስጡ