መጪውን የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከ1 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት እንደተሰራጨ የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡
በዓሉን ምክንያት በማድረግ የዘይት እጥረት እንዳይፈጠር በመዲናዋ ከ1 ሚሊዮን በላይ የፓልም ዘይት እንደተሰራጨ የሚናገሩት የቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ፍሰሃ ጥበቡ፤ ለበአል የሚያስፈልጉ ግብአቶች ላይ እጥረት እንዳይፈጠር በ4 የገበያ ማዕከላትና ከ210 በላይ በሚሆን የሰንበት ገበያዎች በቂ ዝግጅት እንደተደረገ ተናግረዋል፡፡
በቢሮው በኩል ገና ለስርጭት የተዘጋጀ ተጨማሪ ከ200 ሺህ ሊትር በላይ ዘይት መኖሩን የሚናገሩት አቶ ፍሰሃ 1ሺሕ 600 የኡማር ዘይትም እንዳቀረበ አንስተው፤ አሁን ላይ በከተማዋ በቀን ከመቶ ኩንታል በላይ ሽኩርት እየገባ እንዳለነና ከ30 እስከ 55 ብር ድረስ በሰንበት ገበያዎችና በገበያ ማዕከላት እየተሸጠ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በከተማዋ የእንቁላላል አቅርቦት እጥረት ባይኖርም የፍላጎት መጨመር እንደሚስተዋል የገለጹት ሃላፊው የኤልፎራ እንቁላል ከ11 ብር እስከ 13 ብር ድረስ እየተሸጠ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
በንግድ ቢሮ በኩል በቂ አቅርቦት በመኖሩ በከተማዋ የሚገኙ ሸማቾች ተረጋግተው የበዓል ገበያዎችን እንዲያከናውኑ አቶ ፍሰሃ ገልጸው፤ በቁም እንስሳት አቅርቦት በኩልም ዝግጅቶች እየተደረጉ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ