የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክር ኮሚሽን ከህብረተሰቡ ከሰበሰባቸው አጀንዳዎች፣ የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎችን ማስመለስ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት የሚገባው መሆኑን በአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ የተሳተፉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ገልጸዋል፡፡
ተሳታፊዎቹ በህገ መንግስቱ ውስጥ መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች በኮሚሽኑ እንዲታዩ የጠየቁ ሲሆን ሀገራዊ እንድነትን የሚንዱ የሀሰት ትርክቶች መቀረፍ እንዳለባቸው አንስተዋል፡፡
ኮሚሽኑ ከመጋቢት 27 እስከ ሚያዚያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም በአማራ ክልል አጀንዳ ሲያሰባስብ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ በዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማህበረሰቦች፤ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች አጀንዳቸውን ለምክክር ኮሚሽኑ ያስረከቡ ሲሆን፣ በማንነት እና የወሰን ጥያቄዎች ዙሪያ፣ በሰፊው ምክክር መደረግ እንዳለበት ተሳታፊዎቹ አንስተዋል፡፡
በክልሉ ለሚከሰቱ ግጭቶ እና ጦርነቶች ዋነኞቹ ምክንያቶች ያልተመለሱ የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች እንደሆኑ ያነሱት ተሳታፊዎቹ፣ ምክክር ኮሚሽኑ ይህን አጀንዳ ተቀብሎ ለውይይት በማቅረብ መልስ እንዲሰጥበት ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
የማንነት እና የወሰን ጥያቄ፣ የመላው አማራ ህዝብ ጥያቄ እንደሆነ ገልጸው አብዛኛውን የክልሉን ህዝብ ከመንግስት ጋር ያላግባባ በመሆኑ፣ ምክክር ኮሚሽኑ ይህንን ጉዳይ እንደ ትልቅ የቤት ስራ ተቀብሎ እንዲያስፈታ እና በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ትልቁ አጀንዳው ማድረግ እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡
በህገ መንግስቱ መሻሻል ስላለባቸው አንዳንድ አንቀጾች፣ በስፋት እንደተወያዩባቸው እና ለምክክር ኮሚሽኑም የቤት ስራ መስጠታቸውንም በአጀንዳ አሰባሰቡ የተሳተፉ፣ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናግረዋል፡፡
በህገ መንግስቱ የተካተቱ የተለያዩ ትርክቶች እና ትርጓሜዎች ለልዩነት በር የከፈቱ በመሆናቸው፣ አሁን ሀገሪቱ ላለችበት የሰላም እጦት እና ግጭት አድርሰውናል የሚሉት ተሳታፊዎቹ፣ በህገ መንግስቱ የተካተቱ መሰረታዊ ችግሮች በሚገባ መታየት እና መፈተሽ እንዳለባቸው ጠይቀዋል፡፡
በመልከም አስተዳደር እና እኩል ተጠቃሚነት ዙሪያም የሚታዩ ክፍተቶችን መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ፣ ኮሚሸኑ ሰፊ ምክክር አድርጎ ፍሬያማ ውጤት እንዲያመጣ ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ