ጣቢያችን ያነጋገራቸው የከተማ ልማት እና የኪነ ህንጻ ባለሙያ አቶ ቤንጀዲድ ሃይለሚካኤል ለአንድ ከተማ ከሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶች ውስጥ አንዱ የትምህርት ተቋም ቢሆንም እንደሃገር ትምህርት ላይ መሰረት ያደረገ ከተማ እንደሌለን ገልጸዋል፡፡
ቀድሞ የነበሩ ከመሃል ከተማ ወጣ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች በሒደት ከተማ ሲስፋፋ ወደ መሃል ከተማነት እንደሚቀየሩ የገለጹት ባለሙያው፤ ከሌላው ዓለም አንጻር ሲታይ ቀደም ብሎ በእቅድ የተነደፈ ባይሆንም አሁን ላይ ይህ ፕሮጀክት ወደ ተግባር ቢገባ በርካታ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የዜጎችን የመማር ፍላጎት እንደሚጨምር ገልጸው፤ ለተማሪዎች ለጥናት እና ለትምህርት ዘርፉ አጋዥ የሆኑ እንደ ላይብረሪ፤ የምርምር ሳይቶች እና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች ቢካተቱበት ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
በተለይም በከተማዋ ተበታትነው ያሉ ኮሌጆች፤ ላይብረሪዎችን ጨምሮ ሌሎችም በግንባታው ቢካተቱ ተገቢ እንደሚሆን ተናግረው፤ የተመረጠው አከባቢ ከዚህ ቀደም የትምህርት ተቋማት ያለበት በመሆኑ ተገቢ መሆኑንና አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች እንዲኖሩ የሚያበረታታ እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡ እንደዚህ አይነት የመንደር ግንባታዎች ቀደም ብሎ አለመሰራታቸው አሁን ያሉ ነዋሪዎችን የሚያፈናቅል ቢሆንም ከተሞች መልማታቸው የማይቀር በመሆኑ ወሳኔው ተገቢ ነው ብለዋል።
የትምህርት ባለሙያው አቶ መንገሻ አድማሱ በበኩላቸው፤ የዩኒቨርስቲ መንደር በሌሎች የአለም ሃገራት የተለመደ መሆኑን ገልጸዋል። ከሌሎች ሃገራት ልምድ በመነሳት የዩኒቨርስቲ መንደር እንዲመሰረት መወሰኑ ለተማሪዎቹና ለምሁራኑ ብሎም ለትምህርት አሰጣጥ ሂደቱ አጋዥ ነው ብለዋል፡፡
በተለይም ተማሪዎቹ የሚፈልጓቸውን አገልግሎቶች እና የትምህርት ግብዓቶችን ርቀው ሳይይሄዱ በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ ምቹ ምህዳር ይፈጥራል ያሉት ባለሙያው፤ በተጨማሪም የመመረቂያ ጽሁፎችንና የጥናትና ምርምር ውጤቶችን እንዲሁም ግኝቶችን ለገበያው ከማቅረብ አንጻርም ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ከሰሞኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ከአራት ኪሎ እስከ ሽሮ ሜዳ ባለው የከተማው ክፍል የዩኒቨርሲቲ መንደር እንዲመሰረት መወሰኑ የሚታወቅ ነው፡፡
ምላሽ ይስጡ