ሃገሪቱ እ.ኤ.አ ከ1967 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ አገራዊ ቀጥተኛ ምርጫ ለማከናወን እየተዘጋጀች ነው ተብሏል።
ሶማሊያ እሁድ በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ብሔራዊ የመራጮች ምዝገባ ዘመቻ ልታስጀምር መሆኑን መግለጿን የዘገበው አናዶሉ ነው፡፡
በሰኔ መጨረሻ ሊደረግ ከታቀደው የአካባቢ ምርጫ ቀድሞ የሚደረግ እንደሚሆንም ተገልጿል።
የብሔራዊ ገለልተኛ የምርጫና ወሰን ኮሚሽን ሰብሳቢ አብዲከሪም አህመድ ሀሰን በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ የመራጮች ምዝገባ ነገ ማክሰኞ ይጀመራል ብለዋል።
የምዝገባ ማዕከላቱን የጎበኙ የሞቃዲሾ ነዋሪዎች፤ ይህ ከ50 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረግ ነው ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ እ.ኤ.አ. በ2023 ሶማሊያን በጎሳ ላይ ከተመሰረተ የውክልና የድምጽ አሰጣጥ ስርዓት ነጻ እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸውን ዘገባው አስታውሷል።
ካቢኔው ሁለት ረቂቅ ህጎችን ያጸደቀ ሲሆን በ2026 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደሚደረግ ተገልጿል።
የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ሻሪፍ ሼክ አህመድ እና መሀመድ አብዱላሂ መሀመድን ጨምሮ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች የመንግስትን እቅድ ውድቅ አድርገዋል።
እርምጃውን የአንድ ወገን ብለው ጠርተው፤ በትይዩ ድምጽ ማደራጀት እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
እ.ኤ.አ. በ2022 የተካሄደው የመጨረሻው ምርጫ 4.5 ጎሳን መሰረት ያደረገ ስርዓት የተከተለ ሲሆን ይህም ለአራት ትላልቅ ጎሳዎች እኩል የሆነ የፓርላማ ድርሻ የሰጠ እና ለአናሳ ቡድኖች የግማሽ ድርሻን የመደበ ነው።
አገሪቱ እ.ኤ.አ ከ1967 ጀምሮ ቀጥተኛ ምርጫ አካሂዳ እንደማታውቅ ዘገባው ገልጿል።
ምላሽ ይስጡ