በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሚገኘው የጉዛራ ቤተ መንግስት ጥንታዊ እና ታሪካዊ ከሆኑ እንዲሁም በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡ ቅርሶች መካከል አንዱ ሲሆን ቤተ መንግስቱን ከተደቀነበት የመፍረስ አደጋ ለመታደግ የጥገና ስራ የተጀመረ ቢሆንም በአከባቢው ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የጥገና ስራው አለመጠናቀቁን የዞኑ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት እና ፕሮሞሽን ባለሙያ አቶ በላይነህ መንግስቱ እንደሚገልጹት ቤተ መንግስቱን ከመፍረስ አደጋ ለመታደግ በ 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን በጀት ተመድቦለት በአንድ አመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ የጥገና ስራው የተጀመረ ቢሆንም በጸጥታ ችግር ምክንያት ጥገናው አለመጠናቀቁን ተናግረዋል።
የጥገና ስራው ከ50 በመቶ በላይ ላይ መድረሱን የሚናገሩት ባለሙያው የተቋረጠውን የጥገና ስራ ለማስቀጠል እንዲያስችል በአከባቢው ከሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ውይይቶችን በማድረግ ስራውን ለማስቀጠል የሚደረጉ ሙከራዎች መኖራቸውን ነገር ግን የጸጥታ ሁኔታው ስራዎችን በሙሉ አቅም ለመስራት ተግዳሮት እንደሆነ ነው የሚገልጹት።
በዞኑ በርካታ ታሪካዊ እና ጥንታዊ ቅርሶች መኖራቸው የጥገና ስራዎች ብሎም የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናወን የጸጥታ ችግር ተግዳሮት መሆኑ ተገልጿል፡፡
ምላሽ ይስጡ