የአምቦ የገበሬ ኅብረት ሥራ ማኅበር የስንዴ ምርትን ባልተገባ ዋጋ በመሸጥ ከ4 ሚሊየን ብር በላይ አሳጥተዋል የተባሉ የማኅበሩ አመራሮች በጽኑ እስራት ተቀጡ፡፡
በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት፤ ጥፋተኛ የተባሉ የማኅበሩ አመራሮችን በ11 እና በ12 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን ፋሚኮ ዘግቧል፡፡
የዞኑ ዐቃቤ ሕግ የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢና ሥራ አስፈጻሚ ለማ ፈዬ ደገፋ እና የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ የነበረው ታምሩ ታከለ ፊጤ ላይ፤ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1(ሀ) እና የሙስና ወንጀሎች ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 4 ንዑስ ቁጥር 1/4 እንዲሁም አንቀጽ 13 እና ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፋቸውን ጠቅሶ ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸው ነበር።
ተከሳሾቹ ነሐሴ 10 ቀን 2013 ዓ.ም ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ማኅበሩ ለሽያጭ የሚያቀርበውን 12 ሺህ ኩንታል የስንዴ ምርት፤ ሕጋዊ አሠራርን ባልተከተለ መልኩ ለግለሰብ እንዲሸጥ ማድረጋቸው በክሱ ዝርዝር ላይ ተመላክቷል።
በተጨማሪም ገዢው ግለሰብ ማቅረብ የነበረበትን የአምስት ከመቶ ዋስትና ግዴታ በመተላለፍ አንድ ከመቶ ብቻ የዋስትና ግዴታ እንዲያቀርብ በማድረግ፤ ማኅበሩ ለሽያጭ ያቀረበውን የ12 ኩንታል የስንዴ ሽያጭ ዋጋ ቀንሰው እንዲሸጥ በማድረግ ማኅበሩን 4 ሚሊየን 200 ሺህ ብር ማሳጣታቸው ተጠቅሷል።
ተከሳሾቹ ችሎት ቀርበው የቀረበባቸው የክስ ዝርዝር የደረሳቸው ሲሆን፤ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የሰው ምስክርና የሠነድ ማስረጃ አቅርቧል፡፡
ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፤ በተገቢው መከላከል አለመቻላቸውን ጠቅሶ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፏል፡፡
በዚህም የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮ በመያዝ 1ኛ ተከሳሽን በ12 ዓመት እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽን በ11 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡
በተጨማሪም ተከሳሾቹ እያንዳንዳቸውን በ2 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ መወሰኑም ተመላክቷል፡፡
ምላሽ ይስጡ