ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እስኪጠናቀቅ፣ የከተማዋ ነዋሪዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ እና የቦንድ ግዢ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ልዩ ህዝባዊ ንቅናቄ መጀመሩን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡
ግድቡ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ መድረሱ የሚታወቅ ቢሆንም፣ የማጠናቀቂያ ስራዎች ሊዘነጉ የማይገባና ተጨማሪ በጀት የሚያስፈልገው መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ምስክር ነጋሽ፣ የህዳሴው ግድብ በዜጎች ንቁ ተሳትፎ እና ህዝቡ በአንድነት ባበረከተው የማይተካ አስተዋጽኦ ወደ መገባደጃው መድረሱ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው፣ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ በመድረሱ መዘናጋት እንደማይገባ አሳስበዋል፡፡
የሚቀሩ ስራዎች ጥቂት ቢሆኑም ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስፈልጉ በመሆናቸው፣ ማህበረሰቡ እስከመጨረሻው ለግድቡ ሲያደርግ የቆየውን የተለመደ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ከወትሮው በተለየ መልኩ ኢትዮጵያ ችላለች በሚል መሪ ቃል ህዝባዊ ንቅናቄ እያካሄደ መሆኑን የጽህፈት ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ምስክር ነጋሽ ተናግረዋል፡፡ ህዝባዊ ንቅናቄውም በሁሉም ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች እንዲሁም እስከታቸኛው መዋቅር ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
በ14 ዓመት ጉዞው ከአዲስ አበባ ከተማ ማህበረሰብ ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዢ እና በስጦታ መልክ ለግድቡ መሰብሰቡን ዶክተር ምስክር ተናግረዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ