አለም በጉጉት እየጠበቀው የሚገኘው የሁለቱ ቡድኖች ተጠባቂ ጨዋታ ማክሰኞ ምሽት ይከናወናል።
ሻምፒዮኖቹ ሪያል ማድሪዶች ክብራቸውን ለማስጠበቅ በወሳኝ ምዕራፍ ፤ እና አጓጊ ፍጥጫ የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናልን በሩብ ፍፃሜ የሚያገኙ ይሆናል።
መድፈኞቹ አርሰናሎች ምንም በሊጉ ወጥነት ያለው መልካም ውጤቶችን በማስመዝገብ ሊቨርፑል ላይ ጫና ማሳደር ቢሳናቸውም ግን በቀኑ ፤ ጥሩ ሆኖ ምርጥ እንቅስቃሴ ማሳየትን ብቻ በሚጠይቀው በክለቦች ትልቁ የውድድር መድረክ በሆነው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አስደናቂ እንቅስቃሴን በማሳየት ለተከታታይ ሁለተኛ አመት ራሳቸውን የሩብ ፍፃሜ ተፋላሚ ሆነው አግኝተውታል።
በዚህ የውድድር ምዕራፍ ላይ ጥርሱን የነቀለው እና በዚህ መድረክ 15 ጊዜ የነገሰው ሪያል ማድሪድ ምንም በውስጥ ሊግ ያልተጠበቀ ሽንፈት በሜዳቸው ካጋጠማቸው በኋላ ነው ሙሉ ለሙሉ ትኩረታቸውን ወደዚህ ጨዋታ በማዞር ወደ ለንደን የሚያቀኑት።
መድፈኞቹ እ.ኤ.አ ከ2009 ጀምሮ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ አሸንፈው አያውቁም።
ከዚህ በፊት ሁለቱ ቡድኖች እ.ኤ.አ በ2006 ተገናኝተው አርሰናል በደርሶ መልስ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት በማሸነፍ በዛው አመት በሻምፒዮንስ ሊጉ የፍፃሜ ተፋላሚ መሆን መቻላቸው የሚታወስ ነው።
አርሰናል በሻምፒዮንስ ሊግ የውድድር ምዕራፍ በስፔን ላሊጋ እየተሳተፉ ከሚገኙ ክለቦች ጋር ባደረጉቴ ያለፉት 7 ግንኙነታቸው 5ቱን ማሸነፍ ችለዋል። በዚህ አመት ብቻ በሻምፒዮንስ ሊጉ የ8ኛ ዙር ጨዋታ ሂሮናን 2-1 ማሸነፍ መቻላቸው የሚታወስ ነው። በአጠቃላይ በሜዳቸው ከስፔን ተጋጣሚዎች ጋር ባደረጉት ያለፉት 7 ጨዋታዎች 3ቱን አሸንፈው 3ቱን በአቻ ውጤት እንዲሁም 1 ጊዜ ሽንፈት አጋጥሟቸዋል።
በአጠቃላይ የሰሜን ለንደኑ ክለብ በአውሮፓ መድረክ የሩብ ፍፃሜ ደረጃ ላይ ያላቸው ውጤት መልካም አይደለም። 2 ጊዜ አሸንፎ 6 ጊዜ ሸንፈት አጋጥሟቸዋል።
አርሰናሎች በሜዳቸው ያደረጉት ያለፉት 20 ጨዋታዎች ስንመለከት 15ቱን በአሸናፊነት ነው ያጠናቀቁት። በዚ አመት በሜዳቸው ያደረጉትን ያለፉትን 4 ጨዋታ ጎል ሳይቆጠርባቸው ጭምር ነው ያሸነፉት የጥሎ ማለፉ የPSV ጨዋታ 2 አቻ መጠናቀቁ አይዘነጋም።
ወደ ሪያል ማድሪድ ስናመራ ሎስ ብሌንኮሶቹ ከእንግሊዝ ቡድኖች ጋር ከሜዳው ውጪ እስካሁን 10 ጊዜ ሲያሸንፍ 11 ጊዜ ሽንፈት እንዲሁም 6 ጊዜ ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት ነው ያጠናቀቁት።
ማድሪድ ከፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጋር ከሜዳቸው ውጪ ባደረጉት ያለፉት 8 ጨዋታዎች 4ቱን ማሸነፍ ችለዋል። 3ጊዜ ብቻ ነው ሽንፈት ያጋጠማቸው።
በአጠቃላይ ከእንግሊዝ ክለቦች ጋር በደርሶ መልስ ያከናወኑት የሻምፒዮንስ ሊግ መርሀግብር 15 ጊዜ ሲያሸንፉ 7 ጊዜ ብቻ ሽንፈት እንዳጋጠማቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።
በዚህ አመት እንኳን በ5ኛው ዙር አንፊልድ አቅንተው 2-0 በሆነ ውጤት መሸነፋቸው አይዘነጋም።
ማድሪድ በነገሰበት በሚባለው በዚህ በሻምፒዮንስ ሊግ የውድድር ምዕራፍ ላይ ባለፉት 3 ጊዜያት ከወድድሩ የተሰናበተው በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተወካይ ቡድኖች ነው። በ2020/21 የሻምፒዮንስ ሊግ የውድድር ምዕራፍ በግማሽ ፍፃሜው በምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ ከዛ ውጪ በ2019 እና በ2022 ደግሞ በማንቸስተር ሲቲ ከጥሎ ማለፍ እና ከግማሽ ፍፃሜው ውድድር በደርሶ መልስ ተረተው ከውድድሩ ውጪ መሆናቸው የሚታወስ ነው።
ሎስ ብላንኮሶቹ በአውሮፓ በአጠቃላይ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ሲደርሱ ለ40ኛ ጊዜ ነው። በዚ ጊዜ 33ቱን ሲያሸንፉ 6 ጊዜ ብቻ ሽኝፈት አጋጥሟቸዋል። በዚህ አመት በከተማ ተቀናቃኛቸው በአትሌቲኮ ማድሪድ ያጋጠማቸው የ1-0 ሽንፈት ባለፉት 35 ጨዋታቸው 11ኛው ሆኖጰመመዝገቡ የሚታወስ ነው። በዚህ አመት በፈረንሳዩ ተወካይ ቡድን ሊል እና በእንግሊዙ ተወካይ ቡድን ሊቨርፑልም ሽንፈት አጋጥሟቸዋል።
ሪያል ማድሪዶች በሻምፒዮንስ ሊጉ ብቻ ደግሞ ሩብ ፍፃሜ ሲደርሱ ለ21ኛ ጊዜ ነው። ከባየርሙኒክ በመቀጠል ከዚህ ደረጃ የደረሱ ሁለተኛው ክለብ ያደርጋቸዋል።
ከቡድን ዜናዎቻቸው ጋር በተያያዘ ባለሜዳዎቹ አርሰናል ቤት በርካታ ተጫዋቾቻቸው ጉዳት አጋጥሟቸዋል። የመሀል ተከላካዩ ጋብሬል ማጋሌሽ በዚህ አመት ወደ ሜዳ አይመለስም ፤ ከዛ ውጪ በሀገራት የኔሽንስ ሊግ ጨዋታ ላይ ሀገሩ ጣልያንን ወክሎ ጉዳት ያጋጠመው ሪካርዶ ካሊያፊዮሪ በዛሬው ጨዋታ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ነው ተብሏል።
ከዛ ውጪ ቶሚያሱ ፤ ጋብሬል ሄሱስ እና ካይ ሀቨርትዝም ከዚ ጨዋታ ውጪ ናቸው። መልካሙ ዜና ለ3 ወር ከሜዳ ርቆ የቆየው ቡካዮ ሳካ በሙሉ ጤንነት ሙሉ 90 ደቂቃ ተሰልፎ ይጫወታል ተብሎ የሚገመት ሲሆን ቤን ዋይት እንዲሁም ዩሪየን ቲምበር ለጨዋታው ዝግጁ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በእንግዶቹ ማድሪድ በኩል ኦርሌን ቹዋሜኒ በ5 ቢጫ ካርድ ምክንያት በቅጣት በዚ ጨዋታ የማይሰለፍ ይሆናል። ከሱ ውጪ ከሀገራት ጨዋታ በኋላ በክለብ እግርኳስ ያልተመለከትነው ግብ ጠባቂው ቲቦ ኮርቱዋ ያለፉት ሁለት ጨዋታዎች በጡንቻ ህመም ምክንያት አልፈውታል። ለዚህ ተጠባቂ ጨዋታ የመድረሱ ጉዳይ አጠራጣሪ ቢሆንም ከተጓዥ የማድሪድ ቡድን ጋር አብሮ ወደ ሰሜም ለንደን እንደሚያቀና ለማወቅ ተችሏል።
ከዛ ውጪ ፈርላንድ ሜንዲ ፤ ዳኒ ሴባዮስ እንዲሁም ኤደር ሚሊታኦ እና ዳኒ ካርቫሀል ጉዳት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች ስለሆኑ ከዚህ ጨዋታ ውጪ ናቸው።
ይህ እጅግ አጓጊ እና ተጠባቂ መርሀ-ግብር ማክሰኞ ምሽት 4:00 ሲል ከ60ሺ ደጊፊዎች በላይ መያዝ በሚችለው ኤምሬትስ ስቴዲየም የሚከናወን ይሆናል።ጨዋታውን ቦስኒያዊ ዜግነት ያለው ኢርፋን ፔልጅቶ ይመራዋል።
የ40 አመቱ አልቢትር በዚ አመት ማድሪድ ከሌፕዚግ ጋር ያደሰጉትን ጨዋታ በመሀል አልቢትርነት መርቷል። አርሰናል ደግሞ በዩሮፓ ሊጉ ከኖርዌይ ተወካይ ቡድኖች ቦድ ግሊምት እና ሞልደ ከተባሉ ቡድኖች ጋር ያደረጉትን ጨዋታ ዳኝቷል።
የቪድዮ ዳኝነቱ ደግሞ ጀርመናዊው ዳኞው ባስቲናን ዳንከርት እንዲሁም ክሪስቲያን ዲንገርት የሚመራ ይሆናል።
በሚካኤል ደጀኔ
ምላሽ ይስጡ