በኢትዮጵያ የሚገኙ እና ብርቅዬ ያልሆኑ እንዲሁም የመጥፋት አደጋ ያልተጋረጠባቸውን የዱር እንስሳትን አለም አቀፍ ህግና ደንብን በጠበቀ መልኩ በህይወት ለውጭ ሃገር ንግድ እንደሚውሉ እና በአሁኑ ወቅትም በተለያየ ምክንያት በህይወት ያሉ የዱር እንስሳት ንግድ በመቀዛቀዙ የሚፈለገውን ያህል ገቢ እየተገኘ አለመሆኑን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ገልጿል።
በባለስልጣኑ የዱር እንስሳት አጠቃቀም ዴስክ ሃላፊ አቶ ዳንኤል ወርቁ የአዕዋፋት፤ አጥቢ እንስሳት፤ ተሳቢዎችን ጨምሮ ሌሎች የዱር እንስሳትን ወደ ውጭ ሃገር በመላክ ሽያጭ የማከናወን ስራ እንደሚሰራ ገልጸው የመጥፋት አደጋ ያልተጋረጠባቸው እንዲሁም ብርቅዬ ያልሆኑ እንስሳትን በጥናት እና ምርምር በመለየት የንግድ ስራው እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡
ገቢን ከማመንጨት አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታን የሚያስገኙ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ምክንያቶች የዱር እንስሳት ንግድ በመቀዛቀዙ የሚፈለገውን ያህል ገቢ እየተገኘ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ከንግድ ስራው ጎን ለጎን እንስሳቱ ቁጥራቸው እንዳይቀንስ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ የተናገሩት ሃላፊው ለህገ ወጥ ንግድ እና አደን ተጋላጭ የሆኑ እንስሳትን በተመለከተ የተለየ ጥበቃ እንደሚደረግም አንስተዋል።
የዱር እንስሳትን በተለያየ የአጠቃቀም ስልት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባና አንዱ የህይወት ንግድ ሲሆን ካለው ጠቀሜታ አንጻር ዘርፈ ብዙ ስራ መስራት እንዲቻል የህግ ማዕቀፎችን፤ ማሻሻያና ስትራቴጂዎችን የማውጣት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ምላሽ ይስጡ