በሃገራችን ኢትዮጵያ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች እና የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ከሚገኙባቸው አከባቢዎች አንዱ የሃረሪ ክልል ሲሆን የጀጎል ግንብ፤ የጅብ ትርዒት ማሳያ ቦታን ጨምሮ ሌሎች የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን በአዲስ መልክ መታደሱ የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር ማድረጉን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገልጿል።
በክልሉ በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች መኖራቸውን የሚገልጹት የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ አህመድ ናስር በአዲስ መልክ የተሰራው ኢኮ ቱሪዝም ፓርክ እንዲሁም የጅብ ትርዒት ማሳያ ቦታው ላይ ከዚህ ቀደም ትርዒቱን ለመመልከት አመቺ እንዳልነበር ጠቅሰው እድሳት መደረጉ ወደ ስፍራው ተጨማሪ ቱሪስቶች እንዲመጡ ማድረጉን ነው የሚናገሩት።
የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር በርካታ ስራዎች እንደሚከናወን የገለጹት ሃላፊው በክልሉ የሚገኙ ቅርሶች በዓለም ቅርስነት መመዝገባቸው ሐረር የዓለም አቀፍ ቱሪስት ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆንና በክልሉ ያሉ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶችን ቁጥር ማሳደጉንም አክለዋል።
በማይዳሰስ ቅርስነት ከተመዘገቡ ቅርሶች መካከል አንዱ የሆነው የሸዋል ኢድ በዓል ከታሪካዊ ስፍራዎች በተጨማሪ ሌላ የቱሪዝም መዳረሻ መሆኑን ጠቅሰው የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን ለማሻሻል የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ