ኢትዮጵያን ሪድስ ወይም ኢትዮጵያ ታንብብ ከተመሰረተ 22 አመታት ያቆጠረ ሲሆን አላማውም በኢትዮጵያ የንባብ ባህልን ማሳደግ ነዉ፡፡
ህፃናት ከልጅነታቸው የማንበብ ልምድ እንዲኖራቸው የመፅሃፍ አቅርቦትን ማስፋፋት እንዲሁም ለንባብ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር የላቀ ሚና ያለው ሲሆን ይህንንም ለማሳካት ኢትዮጵያን ሪድስ ወይም ኢትዮጵያ ታንብብ ከትምህርት ቤቶች ጋር በጋራ እንደሚሰራ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ታንብብ አስተባባሪ ወ/ሮ ስንታየሁ ዱጋሳ ለመናኸሪያ ሬዲዮ እንዳስታወቁት ለቤተ-መፅሃፍት ግብዓት የሚሆኑ መሳሪያዎችን በድጋፍ መልክ ሲሰጥ መቆየቱን አንስተዉ የህፃናት የንባብ ልምድን ለማሳደግ የተፃፉ የተረት መፅሃፍትን ተደራሽ ለማድረግ የቋንቋ ውስንነቶች በመስተዋላቸው ክፍተቱን ለመቅረፍ በአማርኛ፤ኦሮሚኛ፤ትግርኛ፤ሲዳምኛ፤አፋርኛ እና በሌሎች አምስት ሃገራዊ ቋንቋዎች የተረት መፀሃፍቶች እንደቀረቡ አስረድተዋል።
በጦርነት እና በግጭት ምክንያት ተጎጂ ሆነው ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ህፃናት ለንባብ ያላቸው ፍላጎት እንዳይቀንስ እና እንዳይረሱትም ጭምር እድሜያቸውን ያማከሉ የህፃናት መፅሃፍት ደራሲያን እና ሰዓሊዎች በጋራ በመሆን እያዘጋጁ መሆኑንም አስታወቀዋል።
ኢትዮጵያ ታንብብ አመታዊ ጉባዔ መጋቢት 25/2017 ዓ.ም መከናወኑ ይታወቃል። በመድረኩም ትምህርት ሚንስቴር፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት፤ወመዘክር፤እንዲሁም በርካታ ባልድርሻ አካላት ጋር ምክክር በማድረግ ያልተዳረሱ ትምህርት ቤቶች እና ክልሎች ላይ መጽሃፍትን ተደራሽ ለማድረግ እቅድ መነደፉ ተመላክቷል።
ምላሽ ይስጡ