መጋቢት 24 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)የታላቁ ህዳሴ ግድብ በ14 አመታት የግንባታ ሂደት ከዉጭ የሚደርስበትን ተጽዕኖ ለማርገብ በተለያዩ ቋንቋዎች መረጃዎችን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ውስንነቶች እንደነበሩ የዘርፉ ባለሙያዎች ገልጸዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተመራማሪ እና ተደራዳሪ ፕሮፌሰር አደም ካሚል ባለፉት የ14 ዓመታት ጉዞ ኢትዮጵያ ያላትን የህዝብ ሃብትና ቋንቋ እንዳልተጠቀመችበት ገልጸዋል።
በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተለይም በዲፕሎማሲው ዘርፍ የተሰማሩት እና የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አረበኛ ቋንቋን ባለመቻላቸው ለአረቡ ዓለም ሊገለጹ የሚገባቸው እውነታዎች በአግባቡ አለመነገራቸውን ገልጸዋል፡፡
ፕሮፌሰር አደም ኢትዮጵያ የአረበኛ ቋንቋን ባለመጠቀሟ በአረቡ አለም ለሚኖሩ ወደ 325 ሚሊየን የሚገመቱ ዜጎች ስለ ታላቁ ህዳሴ ግድብ እውነታ እና የኢትዮጵያን አቋም በአግባቡ ማንጸባረቅ አለመቻሉን በቁጭት ገልጸዋል።
ቀደም ሲል የተገለጸውን ሐሳብ የሚያጠናክሩት የአረብኛ ዲጂታል ዲፕሎማሲ ስራ አስኪያጅ እና የኪንግስ ኦፍ አባይ ሚዲያ መስራች ዚያድ ዚዳን ኢትዮጵያ በአረበኛ ቋንቋ አለመስራቷ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ተቀናቃኟ ግብጽ የሔደችበትን ዲፕሎማሲያዊ ርቀት የሚመጥን ስራ እንዳትሰራ አድርጓታል ይላሉ።
ግብጽ ከአረቡ አለም ድጋፍ ለማግኘት ስታሰራጨው የነበረዉን ፕሮፖጋንዳ ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት በትርጉም ስትሰማ እንደቆየች ገልጸዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሃገር የህልውና ጉዳይ በመሆኑ መንግስት አረበኛ ቋንቋን ጨምሮ በተለያዩ የውጭ ቋንቋዎች በትኩረት መስራት እንዳለበት አመላክተዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጨረሻ የግንባታ ምዕራፍ ላይ እንዳለ ይታወቃል።
ምላሽ ይስጡ