የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አደረግሁት ባለው የዳሰሳ ጥናት በመዲናዋ የተወሰኑ የአረንጓዴ ስፍራዎች ለታለመላቸው አላማ እየዋሉ እንዳልሆነ ማረጋገጡን ለጣቢያችን አስታውቋል፡፡
በባለስልጣኑ የስርዓተ ምህዳር እና ብዝሃ ሕይወት አያያዝ ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ይታገሱ በከተማ አስተዳደሩ ማስተር ፕላን ላይ እንደተመላከተው የደን ክልል መሆን ያለበት ቦታ ደን ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስገድድ ቢሆንም በህገወጥ መንገድ ወደ 42 ሄክታር የሚሆን የደንና የአረንጓዴ ስፍራ ከታለመለት አላማ ውጭ ለሌላ አገልግሎት መዋሉን በዳሰሳ ጥናት ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
አቶ ቴዎድሮስ በመዲናዋ ሙሉ በሙሉ ጥናት ቢደረግ መጠኑ ከዚህም ሊጨምር እንደሚችል ነው የገለጹት፡፡ በሌላ በኩል በከተማም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ባለፉት 6 አመታት በርካታ ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰዋል።
በመዲናዋ ባለፈው ግማሽ ዓመት በተተከሉት ችግኞች ላይ በተደረገ የጽድቀት መጠን ቆጠራ በተጠቀሰው ጊዜ ከተተከለው 17 ሚሊዮን ችግኝ 12 በመቶ የሚሆነው መጥፋቱን ገልጸዋል፡፡
ችግኞቹ በእክብካቤ እጦት፤ የተተከሉበት ቦታ ምቹ ባለመሆኑ እና በሌሎችም ምክንያቶች እንደከሰሙ ነው ያስታወቁት።
በመንግስት በኩል በየዓመቱ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ከሚሰሩ ስራዎች አንዱ የችግኝ ተከላ ሲሆን፣ በአንድ ጀንበር በሚሊየን የሚቆጠሩ ችግኞች እንደሚተከሉ፣ የጽድቀት መጠቸውም በየጊዜው እንደሚጠና ገልጸዋል።
ምላሽ ይስጡ