ወደ 25 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ በማድረግ፣ በማቀነባበሪያው የሚያልፉ ወተት እና የወተት ተዋጽኦዎች ጥራታቸው እንዲረጋገጥ እየተደረገ መሆኑን የሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ለመናኸሪያ ሬዲዮ ገልጿል፡፡
የሰበታ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፋብሪካ በሚያመርተው የማማ ወተት፣ ከዚህ ቀደም አንዳንድ የጥራት ችግር ይነሳበት እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ ችግር መቀረፉን የፋብሪካው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ ይመር ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ፋብሪካው ወደ 25 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ በማድረግ ጥራቱን የጠበቀ የወተት ምርት ለህብረተሰቡ እንዲቀርብ የሚያስችል ቤተሙከራ ተገንብቶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚው በፋብሪካው የተገነባው ቤተሙከራ የማማ ወተትን ብቻ ሳይሆን፣ በሀገሪቱ ያሉትን ሌሎች የወተት ምርቶችን ጥራት ማረጋገጥ የሚያስችል አቅም ያለው ግዙፍ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የምርት ብክነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ በተለይ የፋብሪካው ባለሙያዎች በየጊዜው ሙያዊ ስልጠና እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡
በተለይ የጥሬ እቃ ብክነት እንዳይኖር፣ ፍላጎታቸውን ቀድሞ ለአቅራቢዎች በማሳወቅ፣ አስፈላጊው ምርት በአስፈላጊው ሰዓት እንዲቀርብ እንደሚደረግም ነው የጠቆሙት፡፡
የሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ የሚያመርተው ማማ ወተት በዓለም አቀፍ የምግብ ደህንነት ስርዓት ISO 22000/2018 Food Safety Management System እና፣ በዓለም አቀፍ የጥራት ስራ አመራር ስርዓት ISO 9001/2015 Quality Management System የጥራት ማረጋገጫ አውቅና ማግኘቱ ይታወቃል፡፡
ምላሽ ይስጡ