በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ 4 ሰዎችን በሱዳን በኩል ወደ ሊቢያ ከሀገር ለማስወጣት ሲንቀሳቀስ የተገኘ ግለሰብ በ19 ዓመት ፅኑ እስራትና 10 ሺህ ብር እንዲቀጣ ተወስኖበታል።
አቶ አዱኛው ተስፋሁን አዲስ ጥቅምት 17 ቀን 2017 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 9.00 ሰዓት ሲሆን ገንዳ ውሃ ከተማ አስተዳደር ቀበሌ 01 ቀጠና 02 ልዩ ቦታው ቄራ ሰፈር ተብሎ ሚጠራው ስፍራ በህገ ወጥ መንገድ በሱዳን በኩል ወደ ሊቢያ ለማስወጣት በሰሌዳ ቁጥር ኮድ-1 75896 በሆነ ባጃጅ አራት ግለሰቦችን ጭኖ ወደ መሃል ከተማ እያጓጓዘ ሳለ በፀጥታ ሃይሎች ቁጥጥር ሥር ውሏል።
ግለሰቡ በሰው የመነገድና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁ-1178/2012 አንቀፅ 8/1/ ን ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ ወንጀሉን ፈፅሟል።
በፈፀመው ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል የምዕራብ ጎንደር ዞን ፍትህ መምርያ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች የስራ ሂደት ዐቃቤ ህግ በአራት ተደራራቢ የወንጀል ድርጊቶችን መፈፀሙን በመረጃ በማስደገፍ በምዕራብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መስርቶበት ተከሳሹም ክሱ ደርሶት እንዲረዳው ከተደረገ በኋላ በጠበቃ ተወክሎ የተከራከረ ሲሆን ክሱን እንደማይቃወም ነገር ግን የወንጀል ድርጊቱን እንዳልፈፀመ ክዶ ተከራክሯል።
በዚህም ስድስት የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ቀርበው እንደ ዐቃቤ ህግ ክስ አመሰራረት ያስረዱ በመሆኑ ፍ/ቤቱም ተከሳሹ ጥፋተኛ ከመባሉ በፊት የመከላከያ ማስረጃ ካለው እንዲከላከል እድል ቢሰጥም ያቀረባቸው የመከላከያ ምስክሮች ክሱን ማስተባበል አልቻሉም።
ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ከተቀበለ በኋላ በቀን 17/07/2017 ዓ.ም ፍርድ ቤቱ ባዋለው ችሎት ተከሳሹን ያርማል፣ መሰል ወንጀል አድራጊዎችን እና ማህበረሰቡን ያስተምራል የወንጀል ህጉን ዓላማና ግብ ያሳካል ያለውንና እጁ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ የሚታሰብ የ15 ዓመት ፅኑ እስራትና የ10 ሺህ ብር የቅጣት ውሳኔ ማሳረፉን ከምዕራብ ጎንደር ዞን ፍትህ መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ምላሽ ይስጡ