ኢትዮጵያ በአለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ከምታደርገው ጥረት ጎን ለጎን በቴክኖሎጂ የታገዘ የንግድ ስርዓት መገንባት እንደሚገባ ለመናኸሪያ ሬዲዮ የገለጹት በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት እና የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድሙ ፍላቴ ናቸው።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንደ አገር በአለም የንግድ ስርዓት ተወዳዳሪ ለመሆን እያንዳንዱ የንግድ እንቅስቃሴ በዲጂታል በታገዘ መልኩ በኦንላይን ስርዓት የተሳሰረ ለማድረግ፤ በንግድ ስርዓቱ የተሰማራውን አምራች፣ አከፋፋይና ሸማቹን ያስተሳሰረ እንዲሆን እየሰራ ቢሆንም በቂ የሚባል አይደለም ብለዋል፡፡
በይበልጥ ያለውን አሰራር ለማዘመንና በክልሎችም ያሉትን ነጋዴዎችን ጨምሮ እንደሃገር የንግዱን አሰራር ለመቆጣጠር እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ወንድሙ፤ በተለይም የማጭበርበር ተግባርና የምርት ጥራት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ዘመናዊ አሰራርን ለመዘርጋት እየሰራ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፤ የንግዱ ማህበረሰብም ራሱን ለቴክኖሎጂ ክፍት በማድረግ ራስን የማብቃት ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ ተመላክቷል።
ምላሽ ይስጡ