በርካታ የጤና ባለሙያዎችን በማፍራት 102 ዓመታትን ያስቆጠረው የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በ2016 ዓ.ም ባስቀመጠው የ10 አመት የስትራቴጂ ዕቅድ ኮሌጁን ወደ ዪኒቨርሲቲነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች መጀመሩን ገልጿል፡፡
ይሁን እንጅ የባለሙያዎች እጥረት ተግዳሮት እንደፈጠረበት ነው ያስታወቀው።
በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የአስተዳደርና ልማት ምክትል መኮንን እና የህብረተሰብ ጤና መምህር አለሙ ክብረት የኮሌጁን መዋቅር ወደ ዩኒቨርሲቲነት በመቀየር በህክምና፤ በማህበረሰብ ጤና እና በጤና ሳይንስ ዘርፎች ትምህርት ቤቶችን በማቋቋም ከ21 በላይ በሚደርሱ የትምህርት ክፍሎች እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአንዳንድ የትምህርት መስኮች የባለሙያ፤ የመሰረተ ልማት እና ለትምህርት የሚያገለግሉ መሳሪያዎች እጥረቶች ተግዳሮት መፍጠሩን አስታውቀዋል።
የትምህርትና የጤና ዘርፉን በጋራ ለመምራት እንዲሁም የባለሙያ እጥረቱን ለመቅረፍ በሃገር ውስጥ እና ከሃገር ውጪ ከሚገኙ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አቶ አለሙ ተናግረዋል።
ለኮሌጁ ተማሪዎች አገልግሎት የሚውል ቦታ በማዘጋጀት በመሰረተ ልማት ረገድ ያሉ ስራዎችን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የአስተዳደርና ልማት ምክትል መኮንን እና የህብረተሰብ ጤና መምህር አለሙ ክብረት የቦታ ርክክብ እና የግንባታ ፈቃድ ሂደት ማለቁን ተከትሎ ጨረታ በማውጣት በቀጣይ ዓመት ግንባታ ለመጀመር መታቀዱን አስታውቀዋል።
የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የትምህርት እና የጤና አገልግሎት በመስጠት በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንዳለ ይታወቃል።
ምላሽ ይስጡ