የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተለያዩ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ተረፈ ምርቶችን እና ሌሎችም ግብዓቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማድረግ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡
ለአብነትም በአፋር ክልል በስፋት የሚበቅልን አረም ለኢነርጂ አገልግሎት እንዲውል ማድረግ መቻሉን በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ታምርት ፕሮጀክት ፅ/ቤት አስተባባሪ ዶ/ር አያና ዘውዴ ገልፀዋል፡፡ይህንን አረም ለኢነርጂ አገልግሎት ማዋል እንደሚቻል በናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ የፓይለት ሙከራ በማድረግ መረጋገጡን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም መሰረት ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ለሁሉም የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በስፋት የማድረስ እቅድ መኖሩን አብራርተዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ ኢንዱስትሪዎች ከራሳቸው የሚወጣውን ተረፈ ምርት መልሰው ጥቅም ላይ እንዲያውሉ የማድረግ ስራ መጀመሩን ዶ/ር አያና ገልፀዋል፡፡ በተለይም የቆዳ፣የጨርቃጨርቅ እንዲሁም የምግብ ኢንደስትሪዎች ከፍተኛ የሆነ ኬሚካል እና ተረፈ ምርት ያላቸው በመሆኑ አካባቢን እንዳይበክሉ በማድረግ መልሰው ጥቅም እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በስሩ የሚገኙ አምራች ኢንደስትሪዎች ደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻዎችን መልሰው ጥቅም ላይ በማዋል ተጨማሪ ገቢን እንዲያገኙ እንዲሁም ኢንደስትሪዎቹ ባሉባቸው አካባቢዎች ማህበረሰቡ እና አካባቢ ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥሩ ለማስቻል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ምላሽ ይስጡ