ትምህርት መሠረታዊ መብት ብቻ አይደለም ወደ ጤናማ፣ የተረጋጋ እና የበለጸገ ማህበረሰብ የሚወስድ መንገድ ነው ሲሉ የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ራስል ተናግረዋል።
ዩኒሴፍ በታሊባን የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር በሴት ልጆች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ላይ የጣለውን እገዳ እንዲያነሳ ያሳሰበው አዲሱ የትምህርት ዘመን ለሶስተኛ ተከታታይ አመት ያለ ሴቶች ተሳትፎ በመጀመሩ ነው።
“ከሦስት ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ በአፍጋኒስታን ያሉ ልጃገረዶች መብታቸው ተጥሷል ብሏል ድርጅቱ።
ሁሉም ልጃገረዶች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ሊፈቀድላቸው ይገባል፣ ችሎታ ያላቸው ብሩህ ወጣት ሴቶች ትምህርት መከልከላቸው በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ በትውልዱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖው ይፈጥራል ሲሉ የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ራስል ገልጸዋል።
“አፍጋኒስታን ግማሽ የሚሆን ህዝቡን ወደ ኋላ መተው አይችልም ሲሉም አጽዕኖት ሰጥተው ተናግረዋል።
አዲሱ የትምህርት ዘመን ሲጀመር ከ6ተኛ ክፍል በላይ ባሉ ትምህርት ቤቶች ምንም አይነት የሴቶች ተሳትፎ እንደሌለ የገለጸው ድርጅቱ፣ እገዳው ካልተነሳ በ2030 ከ4 ሚሊዮን በላይ ልጃገረዶች ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ውጪ ይሆናሉ ብሏል።
እገዳው በጤና ሥርዓቱ፣ በኢኮኖሚው እና በሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድርም ነው የተገለጸው።
ትምህርት የሚያገኙ ልጃገረዶች ጥቂት በመሆናቸው በልጅነት እድሜያቸው ለጋብቻ የመጋለጥ እድላቸው ከፍ ያለ ሲሆን ይህም በጤንነታቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል ሲል መግለጫው አክሏል።
እገዳው ቢኖርም ዩኒሴፍ በማህበረሰብ አቀፍ ትምህርት ለ445ሺ ህጻናት እድል መስጠቱን ገልጾ፣ ከነዚህም ውስጥ 64 በመቶ የሚሆኑት ልጃገረዶች ናቸው ብሏል።
መግለጫው እገዳው በአስቸኳይ እንዲያነሳ የጠየቀ ሲሆን፣ ትምህርት መሰረታዊ መብት ብቻ ሳይሆን ወደ ጤናማ፣ የተረጋጋ እና የበለፀገ ማህበረሰብ የሚያመራ መንገድ ነው ማለቱን የዘገበው አናዶሉ ነው፡፡
ምላሽ ይስጡ