በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ምክንያት ከ7 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው አለመመለሳቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ፡፡
ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በባሕር ዳር ከተማ የክልሉ የትምህርት ንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ባለበት
ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ምክንያት ከ7 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዳልተመለሱ ገልጸዋል።
ግጭቶች የሕጻናትና ወጣቶችን አዕምሮ በመመረዝ የወደፊት ዕድላቸውን የሚያሰናክሉ በመሆናቸው፤ በአስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጣቸው እንደሚገባ በአጽንኦት አንስተዋል፡፡
ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ በበኩላቸው፥ በክልሉ በትምህርት ላይ የደረሰውን የከፋ ጉዳት በመቀልበስ ወደነበረበት የመማር ማስተማር ሁኔታ ለመመለስ ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በክልሉ በጸጥታ ችግር ምክንያት በዘንድሮው የትምህርት ዘመን 7 ሚሊየን ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ቢታቀድም፤ የተመዘገቡት ተማሪዎች 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ብቻ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ችግሩን ለመቅረፍ በትምህርት ዘመኑ በሁለት ዙር በተደረጉ ኢ-መደበኛ ምዝገባዎች የተመዘገቡት 76 ሺህ ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውን መገለጹን ፋሚኮ ዘግቧል፡፡
ምላሽ ይስጡ