በከተማዋ ባሉት ፏፏቴዎች የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስቡ አድርጎ ለማስቀጠል የማልማት ስራ እየተሰራ እንደሆነ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ ኢንጅነር እንዳሻው ከተማ ለመናኸሪያ ሬዲዮ ገልፀዋል፡፡
አክለውም በከተማዋ ያሉትን ፏፏቴዎች ትኩረት በመስጠትና የጥበቃ ስራውን በመስራት ከዚህ በፊት ይስተዋል የነበረውን የመንገድና የተለያዩ አገልግሎቶችን ችግር በመቅረፍ የከተማዋን ነዋሪና ከከተማ ውጪ የሚመጡ የጎብኝዎችን ቁጥር ለማሳደግ እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡
ፏፏቴዎቹ ሳቢ የሚሆኑት ንጹህ ሲሆኑ ጭምር ነዉ ያሉት ኢንጂነር እንዳሻዉ፤ አሁን ላይ በከተማዋ በሚሰራው የኮሪደር ልማት ተካተዉ ከተፈጥሮ ፏፏቴዎች ባሻገር የሰው ሰራሽ ፏፏቴዎችንም የማስፋት እና ጥቅም ላይ የማዋል አቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ፏፏቴዎቹን አሁን ላይ ለፊልም ቀረጻ፣ ተማሪዎችና የተለያዩ ጎብኝዎች እንደሚጎበኘኟቸዉ ገልጸው፣ በቀጣይ ንጹህና ማራኪ የሆኑ ፏፏቴዎችን የሰው ሰራሾቹን ጨምሮ በማስዋብ የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት ጥቅም ላይ እንደሚያዉሏቸዉ ተናግረዋል፡፡
ማህበረሰቡ በየአካባቢው የሚፈሱ ወንዞችን በመንከባከብና ንፅህናቸውን በመጠበቅ እንደራሱ መጠበቅ እንዳለበትና በመንግስት የሚሰሩ የመዝናኛ ቦታዎቹን በሚገባ መጠቀም እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ