መጋቢት 11 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) እንደ ሀገር ከትምህርት እድል ጋር በተገናኘ ልዩነት መኖሩን የትምህርት ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ከክልል እስከ ከተማ የትምህርት እድል ስርጭት ልዩነት መኖሩን የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከህዝብ ለተነሱ ጥያቄዎች ሚኒስትሮች ምላሽ በሚሰጡበት “እውነት ነው፤ ሐሰት? በተሰኘው መድረክ ላይ አስታውቀዋል።
ከዚህ ቀደም በመንግስትና በግል የትምህርት ተቋማት መካከል ያለው ጥራት እና ስርጭት የሰፋ ልዩነት አልነበረውም ያሉት ሚኒስትሩ፤ አሁን ባለው ሁኔታ ግን እጅግ የተጋነነ ልዩነት እንዳለ ተናግረዋል።
በመሆኑም የትምህርት ዘርፉ ሪፎርም ያስፈለገው መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ልዩነቱን ለማጥበብ አሁን ላይ የመሰረተ ልማት ግንባታና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ እንዳሉ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገልጸዋል።
በትምህርት ፍኖተ ካርታው የትኞቹ አካባቢዎች ምን ያህል የትምህርት ሽፋን ያስፈልጋቸዋል የሚለውን በተማሪ ቁጥር ልክ በየአካባቢው ቅድመ ጥናት ተደርጎ መጠናቀቁን በመግለጽ ከሚመለከታቸው የክልል የትምህርት ቢሮዎች ጋር ምክክር መደረጉን ገልጸዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ህጻን የትምህርት እድል እንዲያገኝ ፍትሃዊ የትምህርት ስርጭትና አገልግሎት ሊኖር እንደሚገባ የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ አሁን ያለው ልዩነት በፍጥነት መቀረፍ እንዳለበት ነው የገለጹት።
የትምህርት እድል እና ጥራትን መፍጠር አዲሱ የትምህርት ሚኒስቴር ሪፎርም ዋነኛ ግብ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰሩ፤ ከሁሉ አስቀድሞ ፍትሃዊ የትምህርት ስርጭት ላይ መስራት ለነገ የማይባል ስራ መሆኑን ገልጸዋል።
ምላሽ ይስጡ