
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ14ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ10ኛ ጊዜ የዳውን ሲንድረም ቀን መጋቢት 28/2017 ዓ.ም “የድጋፍ ስርዓቶቻችን ይሻሻሉ” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር የፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውስንነት ብሄራዊ ማህበር አስታውቋል።
ዓለም አቀፍ ቀኑ፣ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ልጆች በሁሉም መስክ ማካተት እና ስለ መብቶቻቸው ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተገልጿል።
ፍቅር ኢትዮጵያ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ብሔራዊ ማኅበር ቀኑን ምክንያት በማድረግ ከጥቁር አንበሳ እስከ ስታዲየም የሚደረግ የእግር ጉዞ ያዘጋጀ ሲሆን በስታዲየሙ ውስጥም የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ይካሄዳሉም ብሏል።
የቀኑ መከበር የአእምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ልጆች የሚደረገውን ድጋፍ ለማሻሻል እና የሚሰጠውን አገልግሎት ለማስፋት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡
በዘርፉ የተሠሩ ጥናቶች የግንዛቤ ማነስ፣ የአካታች ትምህርት እጦት እና የሲቪል ሰርቪስ ፖሊሲ አለመኖር ዋና ዋና ተግዳሮቶች መሆናቸውን እንደሚያመላክቱ የፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውስንነት ብሄራዊ ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ የሸዋጌጥ ክብረት ተናግረዋል።
ማኅበሩ መንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የአእምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ልጆች የሚሰጡትን ድጋፍ እንዲያሳድጉ ብሎም መብታቸውን ለማስከበር እና ሙሉ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ ለማድረግ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።
ምላሽ ይስጡ