በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከእንደራሴዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት መድረክ፣ በተፈናቃዮች ላይ የሚሰራ ፖለቲካ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የፌደራል መንግስት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ አሁንም ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡
በሰሜኑ ጦርነት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ከመመለስ አንጻር፣ በተለይም በራያ እና ጸለምት መልካም የሚባሉ ስራዎች እንደተሰሩ ገልጸው፣ በወልቃይት ግን በታሰብው ልክ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡
ለዚህም ዋና ምክንያት እና እንቅፋት ፖለቲከኞች ሰብዓዊነት እና ፖለቲካን ቀላቅለው ለተፈናቃዮች ቅድሚያ አለመስጠታቸው እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡
በተፈናቃዮች ስም የሚደረግ የፖለቲካ ጨዋታ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ጠቁመው፣ ፖለቲከኞች ለሰብዓዊነት ቅድሚያ መስጠት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡
ዜጎች ወደ ነበሩበት ቀዬ ተመልሰው የተለመደ ህይወታቸውን እንዲመሩ የፌዴራል መንግስት አሁንም ቁርጠኛ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡
የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ነበሩበት ቀዬ ለመመለስ በሚደረገው ስራ የሚመለከታቸው አካላት ትብብር እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡
ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሰላማዊ ኑሯቸውን መምራት ሲጀምሩ ሌሎች ጉዳዮች በንግግር እና ድርድር እንደሚፈቱም አመላክተዋል፡፡
__
ምላሽ ይስጡ