የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ከሳዑዲ አረቢያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢ/ር ዋሊድ ቢን አብዱልከሪም ኤልኬሬጂ ጋር በጽ/ቤታቸው በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
በውይይታቸው በኢኮኖሚ ዘርፍ ያለውን የሁለቱ አገራት ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ ተነስቷል።ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን በቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ በተለይ ሱዳንን በተመለከተ ከምክትል ሚኒስትሩ ጋር ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ ገለልተኛ አቋም የምታራምድ እና እንደ ጎረቤት እና ወዳጅ አገር ሱዳን ያጋጠማት ችግር እንዲፈታ ወጥ በሆነ መንገድ መፍትሔ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት እንደምትደግፍ ገልጸዋል።
የሳዑዲ አረቢያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢ/ር ዋሊድ ቢን አብዱልከሪም ኤልኬሬጂ አገራቸው የሱዳን ቀውስ መቋጫ እንዲያገኝ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደምትሰራ ገልጸዋል።
በተያያዘ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከሳዑዲው አቻቸው ጋር በሁለቱ አገራት መካከል የኢኮኖሚ ትሰስር በሚጠናከርበት መንገድ፣ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን በጋራ መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች እና ሌሎች የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል በመፍጠሩ የሳዑዲ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ ጠይቀዋል።
የሳዑዲው አቻቸው ኢ/ር ዋሊድ በበኩላቸው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በግብርና ዘርፍ፣ በማዕድን ፣ቱሪዝም እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ ናት ብለዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ አንድ የደኀንነት ስጋት አድርጎ ስለሚወስደው አደጋውን ለመከላከል ከሪያድ ጋር ጠንካራ ትብብር ማድረግ እንደሚፈልግ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ምላሽ ይስጡ