መጋቢት 09 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የሚፈጠሩ አደጋዎችን አስቀድሞ ለመቆጣጠር የቅድመ መተንበያ መሳሪያዎችን ከአጋር አካላትና ከባለሙያዎች ጋር ለመስራት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታዉቋል፡፡ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በሃገሪቱ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት የሚፈጠሩ አደጋዎች ላይ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራ ይታወቃል፡፡
ተቋሙ የአሰራር ሂደቱን ለማሻሻል በተለያዩ አካባቢዎች ካሉ የስነ- ምህዳር ተመራማሪዎችና የሜትሮሎጂ ተቋማት እንዲሁም ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር አስፈላጊ የሆኑ መሳሪያዎችን በማሟላት መረጃ የማጋራት ስራ እንደሚሰሩ የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አለማየሁ ወጫቶ ለጣቢያችን ገልጸዋል፡፡
የሚፈጠሩ አደጋዎችን አስቀድሞ በመተንበይ ህዝቡን ከጉዳት ለመከላከል እንዲቻል በአደጋ ስጋት በኩል ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር አስፈላጊ የሆኑ መሳሪያዎችን በስፋት በማስገባት ለመስራት እንደተዘጋጁ ዶ/ር አለማየሁ አክለው ገልጸዋል፡፡ አደጋን ከሚተነብዩ ከሜትሪዮሎጅ ተቋማት፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ምህዳር ተመራማሪዎች ጋር ተቋሙ በጋራ እንደሚሰራ አክለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽ ለአደጋዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠትና ሰው ተኮር የሆነ ድጋፍ ለማድረግ ስራዎችን የሚያቀልና ተጎጅዎች ላይ ያተኮረ ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡ የሚታወስ ነው፡፡
ምላሽ ይስጡ