ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በፖለቲካዊ ሁኔታዋ ላይ እያለፈች ባለችው ወሳኝ ጊዜ ሚዲያዎች በሃላፊነት እና በተጠያቂነት መረጃ ማቅረብ እንዳለባቸው ምሁራን ለመናኸሪያ ሬዲዮ ገልጸዋል።
በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት መምህር አቶ ገረመው ጫላ እንደገለጹት፣ ሚዲያዎች በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን የመረጃ ፍሰት በሰላማዊ መንገድ በማስተዳደር ለህዝቡና ለሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ደህንነት አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸዉ ጠቁመዋል።
በተለይም ያልተጣሩ መረጃዎችን በማሰራጨት ሃገራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ ከመጣል ፣በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚናፈሱ መረጃዎችን፤ ምንጫቸው የማይታወቅ መረጃዎችን ለህዝቡ ስሜት ቀስቃሽ በሆነ መንገድ ከመዘገብ መታቀብ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል። በዚህ ወቅት የሃገር ሰላም እና የህዝብ ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጥ ሃገራዊ ስክነትን ማምጣት የሚችሉ ዘገባዎች ከሚዲያዎች ተጠባቂ መሆናቸዉን ጠቁመዋል፡፡
የህግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ፣ ሚዲያዎች ያላቸው አቅም በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ እንደመሆኑ እና ከሌሎች ሃገራት ተሞክሮ ተጨባጭ ያልሆኑ መረጃዎች ለሰፊው ማህበረሰብ ማሰራጨት ከወንጀልነቱም በተጨማሪ ሃገረን ለከፍተኛ ቀውስ የሚደርግ በመሆኑ ቆም ብሎ ማሰላሰልን ማስቀድም እንደሚገባቸዉ ተናገረዋል፡፡ ከወገንተኝነት፣ ከተዛቡ መረጃዎችና ከማንኛውም አይነት ተጽዕኖ ነፃ ሆነው መስራት እንደሚገባቸው የህግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ሚዲያዎች በተለይ በዚህ ወቅት የሚሰሯቸዉ ዘገባዎች በሃገር ልማትም ዉድቀትም ላይ አስተዋጽኦ እንዳላቸዉ በመረዳት ሃላፊነት በመዉሰድም ጭምር ሊሆን እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
ምላሽ ይስጡ