ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ተመርጠው ምክር ቤት የገቡ አባላት ባለፉት 4 አመታት የመረጣቸውን ህዝብ ሂደው በአካል ማወያየት እንዳልቻሉ፤ ምክር ቤቱም መፍትሄ ሊሰጣቸው እንዳልቻለ ለመናኸሪያ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
ከሰሞኑ የምክር ቤት አባላት በተመረጡባቸው የምርጫ ክልሎች በመሄድ ህዝቡን ያወያዩ ሲሆን፤ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ እና የቁጫ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲን በመወከል ምክር ቤት የገቡ አባላት ታች ወርደው ህዝቡን ለማወያየት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ /ኢዜማ/ን በመወከል ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዘይሴ ምርጫ ክልል ተመርጠው ምክር ቤት የገቡት አቶ አብርሃም አሞሼ ከ2015 ዓ/ም ወዲህ በተመረጡበት የምርጫ ክልል ሔደው ህዝቡን በአካል አነጋግረው እንደማያቁና ይህን ችግር ምክር ቤቱ እልባት እንዲሰጥ በተደጋጋሚ በጽሑፍና በአካል ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ እንዳላገኙ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደምም ህዝቡን ለማወያየት ወደ ተመረጡበት አከባቢ ቢያቀኑም አካላዊ ጥቃት ደርሶባቸው መመለሳቸውና ክልሉም ይሁን የጋሞ ዞን ችግሩን ሊስቆሙ እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ ከቁጫ የምርጫ ክልል የቁጫ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲን ወክለው ምክር ቤት የገቡት የፓርቲው ፕሬዚዳንት ረዳት ፕሮፌሰር ገነነ ገደቦ ባለፉት 4 አመታት አንድም ቀን የመረጣቸውን ህዝብ ሂደው አወያይተው እንደማያቁና የህዝቡ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ እልባ እንዳልተሰጠው ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፤ እንባ ጠባቂ ተቋም፤ ፍትህ ሚኒስቴር እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጉዳዩን እንዲያቁትና እልባት እንዲሰጡዋቸው ማስታወቃቸውን አመላክተዋል፡፡
የምክር ቤት አባላቱ በዓመት ሁለት ጊዜ በየካቲት ወር እና ሀምሌና ነሀሴ ላይ ህዝቡን በማወያየት ለምክር ቤቱ ሪፖርት እንዲቀርቡ የሚጠበቅ ቢሆንም፤ ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስተያየታቸውን የሰጡ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ግን በተመረጡባቸው አካባቢዎች ሂደው ህዝቡን ማወያየት አለመቻላቸውን ነው ያስታወቁት፡፡
ጣቢያችን በጉዳዩ ዙሪያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ለማናገር ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ምላሽ ይስጡ