በውጭ ቋንቋዎችም ሆነ በሀገር ውስጥ ቋንቋ የሚሰሩ ዘገባዎች የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም ባከበረ መልኩ መሆን እንደሚገባው የሚዲያና የጥናት ተቋማት ለመናኸሪያ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የዲጂታል ሚዲያ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍፁምእሸት ሽመልስ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ ሲሰሩ የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም በመረዳት መሆን እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡
በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ብሔራዊ ጥቅምን አደጋ ላይ የሚጥሉ ዘገባዎች ይሰራሉ ያሉት አቶ ፍጹምእሸት፤ መገናኛ ብዙሃን የሀገራቸውን ብሄራዊ ጥቅምን እንዲረዱ የሚያስችሉ መድረኮችን ማዘጋጀት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከሆርን ሪቪውና ከውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በቀጠናውም ይሁን በዓለም አቀፍ መድረክ የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ማዕከል አድርጎ እንዴት መዘገብ እንደሚገባ ግንዛቤ የሚፈጥር የውይይት መድረክ ማዘጋጀታቸው መልካም ተሞክሮ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሆርን ሪቪው የጥናት ባለሙያው አቶ ፀጋአብ አማረ ተቋማቸው በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን እንደሚያዘጋጅ አስታውቀዋል፡፡
ሆርን ሪቪው ብሄራዊ ጥቅምን መሰረት ያደረጉ ጥናታዊ ዘገባዎችን እየሰራ እንዳለም ነው የተናገሩት፡፡ ባለሙያው በውጭ ቋንቋዎች የሚሰሩ የሀገርን ገጽታ በበጎ የሚገልጹ እና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብሩ ዘገባች እጅግ አነስተኛ መሆናቸውን ነው የሚገልጹት፡፡
በቀጣይም ገለልተኛ የሆኑ የሀገርን ጥቅም ማዕከል አድርገው የሚሰሩ መገናኛ ብዙሃን መበራከት እንዳለባቸው እና ከጎረቤት ሀገራትም ልምድ መውሰድ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
መገናኛ ብዙሃን በሚሰሯቸው ማንኛውም ዘገባዎች ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ማድረግ እንደሚገባቸው ባለሙያዎቹ ገልጸዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ