በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአሪና ደቡብ ኦሞ ዞኖች አዋሳኝ ያለው የታማ ማህበረሰብ ጠብቅ ደን፣ በዙሪያው ባሉ አራት ብሄረሰቦች እንዲጠበቅ፣ ከአንድ ወር በፊት መግባባት ላይ መደረሱን ታዉቋል፡፡
በዚህም የአራቱም ብሄረሰቦች ህዝቦች በባለቤትነት ደኑን በጋራ መጠበቅ የሚያስችል ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን፣ ከአራቱም ብሄረሰቦች የተወጣጣ ስካውት ተቋቋሞ፣ ደኑን በጋራ የመጠበቅ እና የመንከባከብ ስራ እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና ቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ገልገሎ ገልሾ ናቸው፡፡
በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙት ቦዲ፣ ሙርሲና ባጫ ብሄረሰቦች እንዲሁም፣ በአሪ ዞን የሚገኘው አሪ፣ ብሄረሰብ ባጋራ ለመጠበቅ ተስማምተው፣ ህጋዊ የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረሙበት የታማ ማህበረሰብ ጥብቅ ደን፣ በየጊዘው በርካታ ቱሪስቶች ከሚጎበኗቸው በክልሉ ካሉ የቱሪስት መዳረሻዎች አንዱ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በጥብቅ ደኑ ዙሪያ የሚኖሩ እነዚህን የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ እና፣ በባለቤትነት እንዲጠብቁት ለማድረግ፣ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር ጥናት ሲያደርግ ቆይቶ፣ አራቱም ብሄረሰቦች በጋራ እንዲጠብቁት የጋራ መግባቢያ ሰነድ አዘጋጅቶ፣ እንዲፈራረሙ ማድረጉንም አመላክተዋል፡፡
በፌዴራልና በክልሉ በበላይነት የሚታዳደሩ፣ ሌሎች በርካታ ፓርኮች እና የቱሪስት መዳረሻዎች በክልሉ ያሉ መሆናቸውን አንስተው፣ የታማ ማህበረሰብ ጥብቅ ደን ማህበረሰቡ የሚያስተዳድረው መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ በጥብቅ ደኑ ዙሪያ ያሉ አራቱም ብሄረሰቦች ቀድሞውንም በርካታ ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶቻቸው የተቀራረቡ በመሆናቸው፣ ደኑን በጋራ እንዲጠብቁት እና እንዲጠቀሙበት መደረጉ የማህበራዊ ቁርኝታቸውን ይበልጥ እንደሚያጠናክርም ገልጸዋል፡፡
በአካባቢው የታማ ማህበረሰብ ጥብቅ ደን መኖሩ ሌሎች የማህረሰቡ መለያ የሆኑ ባህላዊ እሴቶች እንዲገበኙ እድል ይፈጥራል ሲሉም አቶ ገልገሎ አክለዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ