የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ ለአማራ ክልል የሚያስፈልገዉን የማዳበሪያ መጠን መላኩን አስታዉቋል፡፡
በአማራ ክልል ያሉ አርሶ አደሮች ለመናኸሪያ ሬዲዮ ባሰሙት ቅሬታ፤ መጪው የበልግ የዝናብ ወቅት በመሆኑ ዝናቡን በመጠቀም ምርታማ የምንሆንበትን ዝግጀት ያደረግን ቢሆንም እስካሁን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት አልደረሰንም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ባሉ የወረዳ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ለአርሶ አደሩ የተመደቡ ማዳበሪያዎች እያሉ እኛ ጋር እንዳይደርስ በመታገዱ እንዳለፉት አመታት ምርታማ ለመሆን አልቻልንም ፈተና ላይ ነንም ሲሉም አክለዋል፡፡ የሚመለከታቸውን አካላት የጠየቁ መሆኑንና ማዳበሪያው ይመጣል ከሚል ምላሽ ያለፈ የተሰጣቸው ተጨባጭ ነገር አለመኖሩን አንስተው የሚመለከተው አካል ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል ።
የግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ከበደ ላቀው በበኩላቸው በ2017/18 የበጀት አመት አስፈላጊው የማዳበሪያ ግብዓት ከውጪ ግዢ መፈጸሙንና ወደሃገር ወስጥ ለማስገባት የማጓጓዝ ስራ አሁንም መቀጠሉን ተናገረዋል፡፡
አሁን ላይ በቂ የሚባል የማዳበሪያ ግብዓት በሃገሪቱ እንዳለና ክልሎች የተመደበላቸውን የአፈር ማዳበሪያ ኮታ ከማዕከላዊ መጋዘን በክልሉ የህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት እየወሰዱ መሆኑን የሚገልጹት ሃላፊው ፤ በሚኒስተሩ በኩል የገጠመ ችግር አለመኖሩን አስረድተዉ አርሷደሩ ጋር ያልደረሰበትን ምክንያት የክልሉ ግብርና ቢሮ ማብራሪየ መስጠት እንዳለበት ጠቁመዋል ።
መናኸሪያ ሬዲዩ በጉዳዩ ላይ የአማራ ክልል የግብርና ቢሮን ለማነጋገር ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት ባለመሳካቱ በክልሉ የተፈጠረውን ክፍተት በቢሮ በኩል ምላሽ ማግኘት አልቻለም፡፡
ምላሽ ይስጡ