መምህራንን የቤት ባለቤት ለማድረግ የማደራጀት ስራ እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መምህራን ማህበር ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል።
የቤት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ በማደራጀት ስራው እስካሁን ከ23ሺሕ በላይ መምህራን መመዝገባቸውን የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ድንቃለም ቶሎሳ ተናግረዋል። ካሁን ቀደም የነበረው የማደራጀት ስራ መምህራኑ 70 በመቶ ያህል ቆጥበው ቀሪውን 30 በመቶ ቤቱን ካገኙ በኋላ የሚያስቀጥሉበት አግባብ እንደነበር የገለጹት ፕሬዝዳንቱ አሁን ላይ ግን 30 በመቶ ያህሉን ብቻ ቆጥበው የቤት ባለቤት እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
ምንም እንኳን 30 በመቶውንም ለመቆጠብ ለመምህራን አዳጋች ቢሆንም ለጊዜው ያለውን አማራጭ እንዲጠቀሙ በማድረግ በቀጣይ የተሻለ አማራጭ የሚፈለግ ይሆናል ሲሉ አቶ ድንቃለም ገልጸዋል።
በመሆኑም ያልተደራጁ መምህራንን በአደረጃጀት ውስጥ በማስገባት የመምህራንን የቤት ችግር ለመቅረፍ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ቀሪ የማደራጀትና የመመዝገብ ስራዎች እንደሚከናወኑና በያዝነው አመት ቀሪ ጊዜያት ውስጥ ቀዳሚ ትኩረታቸው እንደሆነ ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል። አሁን ላይ ከንግድ ባንክና ከቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር እየሰሩ እንደሚገኙም አቶ ድንቃለም አክለው ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከማስተማር ስነ-ዘዴ ጋር በተገናኘ የታቀዱ የመምህራን የደረጃ እድገት እቅዶች አሉ በማለት ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌደራልና ከተማ አስተዳደር ውይይትና ውሳኔ የሚፈልጉ ስለመሆናቸው ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ምላሽ ይስጡ