ወጣቱን በዲፕሎማሲው ዘርፍ ለማብቃት ወጥ እና ተከታታይነት ያለው ስልጠናዎችን መስጠት፤ ተቋማትንም ማደራጀት ይገባል ተብሏል፡፡
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲ እና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ አበራ ሄጲሶ የዲፕሎማሲው መስክ ሁለት ነገሮችን አብዝቶ የሚሻ ነው ይላሉ፡፡ በአንድ በኩል ሙያን መሰረት ያደረጉ እንቅስቃሴዎችን የሚፈልግ ሲሆን፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ብሄራዊ ጥቅምን መሰረት ያደረገ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡
ሀገሪቱ በዲፕሎማሲያው መስክ ጠንካራ አቅሟን በአለም አደባባይ በስፋት እንድታሳይ ያደረጋት መልካምድራዊ አቀማመጧ እና በፖለቲካው መስክ ያላት ከፍታ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በይደር የተቀመጡ የቤት ስራዎችን ለመስራት በሀገሪቱ የወጣት ዲፕሎማቶችን ቁጥር ማሳደግ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
ለሙያው በቂ የትምህርት ዝግጅት ያላቸውን ማሳተፍ ለዚህም ደግሞ ወጣት ዲፕሎማቶችን ማብቃት የሚያስችል ማሰልጠኛ ተቋማትን ማስፋፋት ይገባል ብለዋል፡፡
በዲፕሎማሲው መስክ ከ30 አመታት በላይ ኢትዮጵያን ያገለገሉ እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ በዲፕሎማሲው መስክ የሰሩት ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና በዲፕሎማሲው መስክ ለመሳተፍ የሚሹ ዜጎች የሀገር ፍቅርን፤ የሀገር ግንባታን እንዲሁም ሀገሪቱ የምትከተላቸው ፖሊሲዎችን በአግባቡ ማወቅ እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡
በዚህም ወጣቱን በዲፕሎማሲው ዘርፍ ለማሳተፍ በቅድሚያ ወጣቱ ያለውን ዝንባሌ፤ ግንዛቤ እንዲሁም የቋንቋ ችሎታ ማጤን ይገባል ባይ ናቸው፡፡ እነኚህ መስፈርቶችን የሚያሟሉትን እና ፍላጎቱም ያላቸውን ሊያሰለጥኑ የሚችሉ በቂ ተቋማት መገንባት እንዳለባቸው አመላክተዋል፡፡
ሀገራት በዲፕሎማሲው ረገድ ጠንካራ እንዲሁም ሞጋች የሆነ አሰራርን መተግበር እንዲችሉ በዘርፉ የሚሳተፉ አካላት ብቃት እና ሚናቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ምላሽ ይስጡ