ኢትዮጵያ ተተኳሽ ጥይቶችንና ወታደራዊ ድሮኖችን በራሷ ማምረት በመጀመሯ በአገሪቱ የኢኮኖሚና የፀጥታ ሁኔታ ላይ አዲስ ምዕራፍ መከፈቱን የቀድሞ ዲፕሎማት እና የቀድሞ ኢትዮጵያ ሰራዊት አባል ለመናኸሪያ ሬዲዮ ገልጸዋል።
ይህ እርምጃ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ጫና ከማቃለል ባለፈ ምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ላይ አቅምን ለማጎልበት እንደሚረዳ፤በተለይም ኢትዮጵያ ወታደራዊ አቅሟን በማሳደግ በቀጣናው ያላትን ተሰሚነት የምታሳድግ ከመሆኑም በላይ ቀጠናዊ ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርጋት መሆኑን የቀድሞ ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ለጣቢያችን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የጦር መሳሪያ ማምረት መጀመሩ አዲስ ባይሆንም ነገር ግን አሁን ላይ በተጠናከረ ደረጃ በስፋት ከመጀመሩም ባለፈ ለውጪ ገበያ መቅረቡ በሃገር አቀፍ ደረጃ በወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች ላይ ከፍተኛ ስኬት መሆኑን ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ ለጦር መሳሪያ ግዢ የምታወጣውን ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ ጫናን የሚቀንስ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ሃሳባቸውን ለመናኸሪያ ሬዲዮ የገለጹት የቀድሞ ኢትዮጵያ ሰራዊት የድጋፍ እና ልማት ማህበር ፕሬዝዳንት 50 አለቃ ብርሃኑ አማረ ፣ለአንድ ሃገር ወታደራዊ ጥንካሬ መኖር ሁለንተናዊ ስኬታማነት ለማረጋገጥ የሚረዳ እንቅስቃሴ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በዋናነት ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ላይ ትኩረት የሚደርግ ቢሆንም በወታደራዊ ስርዓት በኩል የሚኖር የአቅም ማጎልበት እና ዘመናዊ መሳሪያዎችን እንዲሁም ግብዓቶቻቸውን በራስ አቅም ማምረት መቻል እንደ ታላቅ ሃገር እና በምስራቅ አፍሪካ ብሎም በአለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነት የሚጨምር ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የጦር መሳሪያ ማምረት መጀመሩ ለሀገሪቱ እድገት አዲስ ምዕራፍ ሲሆን እነዚህ እንቅስቃሴዎች በማጠናከር ወታደራዊ ፍላጎትን ከማሟላት በተጨማሪ በአለም አቀፍ ደረጃ ምርቶችን በተወዳዳሪነት ማቅረብ ላይ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ