በከተማው የሚስተዋለውን የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት በማሰብ ለዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ የተከፈተው የሸገር ዳቦ ፋብሪካ በቀን እስከ 1.5 ሚሊዮን ዳቦ የማምረት አቅም ያለው ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች የማምረት ስራው ተቋርጦ እንደነበር የሚታወቅ ነው።
ከጥቅምት 23/2016 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ መልክ ማምረት የጀመረ መሆኑንና በአሁኑ ወቅት፤ በቀን 1 ሚሊየን ዳቦ በማምረት በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ጭምር ለምገባ አገልግሎት እየተሰራጨ እንደሚገኝ የገለጹት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የገበያ ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መከታ አደፍሬ ፋብሪካው ካለው የማምረት አቅም አንጻር አሁን ላይ እያመረተ የሚገኘው ምርት በቂ አለመሆኑን ጠቅሰው በህብረተሰቡ በኩል ምርቶቹን የመግዛት ፍላጎት መቀነስ፤ ሌሎች የምርት አቅርቦት አማራጮች እንዲሁም በተለያየ ጊዜ የሚያጋጥሙ ብልሽቶች በምክንያትነት የሚጠቀሱ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከምርት ጥራት እና መጠን ጋር በተያያዘም ከመጀመሪያ የምርት ሂደት ጀምሮ በተከታታይ እስከ መጨረሻው የምርት ውጤት ድረስ ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግ ያነሱት ዳይሬክተሩ ከጥራት ጉድለት ጋር በተያያዘ ባለፉት 7 ወራት ከማህበራት የመጡ ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ በተወሰደው እርምጃ የታዩ የጥራት ጉድለቶች እንዲስተካከሉ መደረጉን እና ለማንኛውም የዳቦ አምራች በተቀመጠው የግራም መጠን መሰረት ቁጥጥር እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ዳይሬክተሩ አያይዘውም ከመሸጫ ቦታዎች ጋር በተያያዘም ህጋዊ አሰራሩን በጠበቀ መልኩ የገቢ አቅምን ማሳደግ የሚያስችሉና ከዳቦ ምርት ሽያጭ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ሌሎች ተጓዳኝ ስራዎች እንዲሰሩ የሚደረግበት አግባብ መኖሩን ነው የተናገሩት።
የሸገር ዳቦ ፋብሪካ በቀን ያመርታል ተብሎ በተቀመጠዉ ቁጥር ልክ ለምን ማምረት አልቻለም የሚለዉን ምላሽ እንዲሰጡን ለሸገር ዳቦ ፋብሪካ አመራሮች ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪዎችን ብናደርግም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም፡፡
ምላሽ ይስጡ