የመምህራን የገቢ ምንጭና አቅም አነስተኛ መሆኑ ቢታወቅም መርህን ለመከተል ያህል ሃብት ማስመዝገቡ ተገቢ መሆኑን የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አስታውቋል።
መምህራን ከእለት ገቢ ተርፎ እንደ ሃብትነት የሚመዘገብ ገቢ እንደሌላቸው እና ይህንኑ እውነታም አስመዝግቡ የሚለው አካል እንደሚያውቀው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አበበ ለመናኸሪያ ሬዲዮ ተናግረዋል።
ነገር ግን በመርህ ደረጃ ሁሉም ዜጋ ያለውን ሃብት እንዲያስመዘግብ በሚለው አሰራር መሰረት የተጠየቀ በመሆኑ መምህራን ያላቸውን ወርሃዊ ገቢም ቢሆን እንዲያስመዘግቡ መጠየቁ ተገቢነት ሊኖረው ይችላል ሲሉ አቶ ሽመልስ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የመምህርነት ሙያ በትምህርት ዝግጅትም በጥራትም ልዩ ክትትል እንደሚፈልግ በማሳወቅ ማህበሩ ክትትል እያደረገ ቢሆንም በተለይ በአሁኑ ሰዓት በርካቶች ወደ መምህርነት ሙያ ለመሰማራት ፍላጎት ስለሌላቸው እና ሙያውን የሚመርጡ ባለሙያዎች ቁጥር በእጅጉ እየቀነሰ በመምጣቱ ተግዳሮት መፈጠሩን የማህበሩ ምክትል ፕሬዝደንት ተናግረዋል።
በተለይ በለጋ እድሜያቸው ወደ መምህርነት ሙያ እንዲሰማሩ የሚያደርገውን አሰራር ለማስቀረት የነበረው ፍላጎት ዘርፉ ተመራጭ ባለመሆኑ ምክንያት ለክትትል አመቺ እንዳልሆነ አቶ ሽመልስ ተናግረዋል።
የመምህርነት ሙያ በአግባቡ ቦታ ተሰጥቶት ጥራቱን ከመከታተል አንጻር ልዩ ክትትል ቢፈልግም ሁኔታዎቹ ሳይሟሉ እየቀጠሉ እንዳሉ የገለጹት የማህበሩ ምክትል ፕሬዝደንት አሁንም ዘርፉ ከመንግስት ልዩ ድጋፍ እንደሚፈልግ ተናግረዋል።
ምላሽ ይስጡ