የካቲት 28 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች የሚገነባው የኮሪደር ልማት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ መሆን እንደሚገባው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ለመናኸሪያ ሬዲዮ ገልጿል፡፡
አካል ጉዳተኞች በተለያዩ አገልግሎቶች እና መሰረተ ልማቶች በፍትሐዊነት ተጠቃሚ መሆን ሲገባቸው፤ ህጎችና መመሪያዎች በተጨባጭ ባለመተግበራቸው ተጠቃሚነታቸው ዝቅተኛ መሆኑን በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶች፣ ህጻናት፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገ/ሃዋርያት ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የሚሰጡ አገልግሎቶች እና የሚገነቡ መሰረተ ልማቶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አለመሆናቸውን የሚገልጹ በርካታ ቅሬታዎች ለኮሚሽኑ እንደሚደርሱት አስታውቀዋል፡፡
ግንባታዎቹ ዊልቸር እና ሌሎች የአካል ድጋፎችን ለሚጠቀሙ አካል ጉዳተኞች አመች እንዳልሆኑ ነው ኮሚሽነር ርግበ ገ/ሃዋርያት የገለጹት፡፡
በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች እየተገነቡ ያሉት የኮሪደር ልማት ስራዎች በመንግስት በኩል አካታች ናቸው ይባል እንጅ ኮሚሽኑ ከአካል ጉዳተኞች ማህበራት ጋር በመሆን ባደረገው ግምገማ አካታች አለመሆናቸውን አረጋግጣል ብለዋል፡፡
አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ከግንባታቸው ጀምሮ የሚስተዋለው ክፍተት ሰፊ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ርግበ፣ በኮሚሽኑ በኩል ሙሉ በሙሉ እንዲተገበርና አካታች እንዲሆን ጥረቶች እንደሚደረጉ አመላክተዋል፡፡
የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ የሁሉም ማህበረሰቡ ጉዳይ እንደሆነ በመረዳት በተለይ በአገልግሎት መስጫ ቦታዎች ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር የትምህርት ተቋማትና ጉዳዩ በቅርበት የሚመለታቸው አካላት ስለ አካል ጉዳተኞች ያለውን ግንዛቤ ከማስፋፋት አንጻር ከፍተኛ ድርሻ እንዳለባቸውም አመላክተዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ