የከፍተኛ ሃይል ተጠቃሚ ለሆኑ ደንበኞች የቆጣሪ ቅያሪ ለማድረግ እቅድ ተይዞ ሲሰራ መቆየቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡
በዚህም መሰረት በሀገሪቱ ለሚገኙ የከፍተኛ ሃይል ተጠቃሚ ደንበኞች የስማርት ቆጣሪ ቅያሪ ገጠማ መደረጉን የገለፁት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ታዬ ናቸው፡፡
ተቋሙ እያደረገ ካለው አሰራሩን የማዘመን ስራ ጋር አብሮ የቆጣሪ ማዘመን ስራዎችን በመስራት ከዚህ በፊት የሚነሱ ቅሬታዎችንም ጭምር ለመቅረፍ የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በተለይም ደግሞ ቤት ለቤት በሚደረግ ቆጠሪ ከክፍያ ጋር የተያያዙ ቅሬታዎች በስፋት የሚነሱ በመሆኑ እነዚህ የስማርት ቆጣሪዎች ቀን በቀን ምን ያህል እንደተጠቀሙ ለተጠቃሚዎችም እንዲሁም ለተቋሙ መረጃ የሚሰጥ በመሆኑ ችግሩን ከመቅረፍ አኳያ ትልቅ ሚና እንዳለው አንስተዋል፡፡
እንዲሁም ብልሽት እና የሃይል መቆራረጥ ሲኖር በቀላሉ ማወቅ እንዲቻል የሚረዳ በመሆኑ አፋጣኝ ጥገና እንዲሰጥ እንደሚያደርግና ፤ አሁን ላይም ከከፍተኛ ሃይል ተጠቃሚ ደንበኞች ባለፈ ወደ ዝቅተኛ ሃይል ተጠቃሚዎችም ቅያሪውን ማድረግ መጀመሩን አቶ መላኩ ገልፀዋል፡፡
ቆጣሪ መነካካት ፣ከቦታ ቦታ መቀየር እንዲሁም የሃይል ስርቆት ለማድረግ መሞከር እና ሌሎችም በስፋት የሚስተዋሉ ችግሮች በመሆናቸው ከተቋሙ ባለሙያዎች ውጪ የሚፈፀሙ ተግባራት በህግ አግባብ ተጠያቂ የሚደርግ ሲሆን ስማርት ቆጣሪዎቹ ይህንንም የሚቀርፉ በመሆናቸው በስፋት የማዳረስ ስራ እንደሚከናወን ተመላክቷል፡፡
ምላሽ ይስጡ