አግባብነት ካለው አካል የተሰጠን የተሽከርካሪ መለያ ሰሌዳ ቁጥር በሚታይና ግልፅ በሆነ መልኩ በተሽከርካሪው አካል ላይ መለጠፍ እንደሚገባ በአዋጅ ተደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል አሽከርካሪዎች የተደመሰሰ፣ የታጠፈ ፣ የተፋፋቀ፣ የተቆራረጠ እና በአጠቃላይ ለዕይታ ግልፅ ያልሆነ ሰሌዳን በመጠቀም ደምብ ሲተላለፉ ቆይተዋል፤ አንዳንዶቹም ደምብ መተላለፉን እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ወንጀል ሲፈፅሙ የተገኙ ተይዘው ምርመራ እየተጠራባቸው መሆኑን ፖሊስ ገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ የተሽከርካሪን መለያ ሰሌዳ ቁጥር ያላግበብ የሚጠቀሙ አካላትን ለመቆጣጠር ከየካቲት 16 እስከ የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ/ም በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች በቀንንና በማታ ባደረገው ቁጥጥር በአዋጅ ከተደነገገው ውጪ የተሽከርካሪ መለያ ሰሌዳ ቁጥርን ያለ አግባብ ሲገለገሉ በተገኙ1,587 ደንብ ተላላፊዎች ላይ በትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ መሰረት እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡
የተደመሰሰ ፣ የተፋፋቀ፣ የደበዘዘ፣ የታጠፈ እና የማይታይ የተሽከርካሪ መለያ ሰሌዳ ቁጥር መጠቀም፣ ከሰሌዳ መብራት ውጪ ሌሎች ዓይነቶችን አብረቅራቂ መብራቶችን መጠቀም፣ ሰሌዳውን በማይታይ ቦታ መለጠፍ እና ሆን ብለው ሰሌዳን አጥፎ መንቀሳቀስ በቁጥጥሩ ወቅት የተገኙ ጥፋቶች ናቸው፡፡
በጥፋት ውስጥ ከተገኙት ውስጥ ኮድ-1 ወይም ታክሲ 216፣ ኮድ-2 ወይም የቤት መኪና 320፣ ኮድ-3 የሆኑ 1,037 እና ሌሎች ተሽከርካሪዎች 14 መሆናቸውን በአዲስ አበባ ፖሊስ የትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ አስታውቋል፡፡
በአጠቃላይ ቁጥጥር ከተደረገባቸው መካከል ዘጠኝ መቶ ሃምሳ አምስቱ የፊት ወይም የኋላ ሰሌዳ ሳይኖራቸው የተገኙ ሲሆን ቀሪዎቹ 633ቱ ደግሞ የተደመሰሰ፣ የተቆረጠ ወይም ለዕይታ ግልጽ ያልሆነ ሰሌዳ ሲጠቀሙ የተገኙና ሰሌዳውን በማይታይ ቦታ ያሰሩ፣ የተሸፈኑና የተለያየ ቀለም የተቀቡ ሰሌዳዎች መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
የተሽከርካሪ መለያ ሰሌዳ ቁጥርን በማይታ ቦታ ላይ ያሰረ፣ የተደመሰሰ ወይም የተቆራረጠ፣ የተሸፈነ እና ሰሌዳውን ቀለም የቀባ እንዲሁም የፊት ወይም የኋላ ሰሌዳ ሳይኖረው ያሽከረከረ በቅርቡ ተግባራዊ በሆነው ደምብ ቁጥር 557/2016 መሰረት የሚያስቀጣ ደምብ መተላለፍ መሆኑን ተደንግጓል። አዲስ አበባ ፖሊስም በደንብ ተላላፊዎች ላይ እያደረገ ያለውን ቁጥጥር አጠናክሮ እንደሚቀጥል እያስታወቀ የተሽከርካሪ ባለ ንብረቶች ሆኑ አሽከርካሪዎች በተሽከርካሪ መለያ ሰሌዳ ቁጥር አጠቃቀም ዙሪያ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡
ምላሽ ይስጡ