የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከዚህ ቀደም ባልተደረገባቸው 10 ክልሎች የተካሄደ ሲሆን ከተቀመጠው እቅድ በላይ ከ5 ዓመት በታች ያሉ ህፃናት መከተባቸውን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡
የክትባት ዘመቻው ለ4 ቀናት ተብሎ ቢጀመርም በአንዳንድ አካባቢዎች ዘግይተዉ የጀመሩ በመኖራቸው እና ተጨማሪ ቀናት ለሚያስፈልጋቸው ክትባቱ እንዲቀጥል በመደረጉ በ4ቱ ቀናት ከ13 ነጥብ 86 ሚሊየን የነበረው ቁጥር ወደ 14 ነጥብ 97 ሚሊየን ከፍ ማለቱን በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የፖሊዮ ወረርሽኝ ምላሽ አስተባባሪ አቶ ሚኪያስ አላዩ ገልጸዋል፡፡
በዘመቻው ወቅት ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸውንም ህፃናት የመለየት ስራ የሚከናወን በመሆኑ ክትባቱ በተሰጠባቸው አስሩም ክልሎች ከ1 ሺህ 5 መቶ በላይ የእግር መዞር እክል ያለባቸው ህፃናት መገኘታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ማህበረሰቡ የእግር መዞር የጤና እክል ላይ ያለው ግንዛቤ ከዘር፣ከእርግማን እና ሌሎችም ጉዳዮች ጋር የሚያያዝ አድርጎ የማሰብ ሁኔታ መኖሩን እና በሽታውም በተፈጥሮ የሚመጣ ስለመሆኑ እንጂ ምክንያቱ በጥናት አለመረጋገጡን በመጥቀስ ኢንስቲትዩቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ለኩፍኘ በሽታ በተሰጠ የክትባት ዘመቻ ከ3000 በላይ የሚደርሱ ህፃናት የእግር መዞር በሽታ እንደተገኘባቸው የጠቀሱት አቶ ሚኪያስ በቀጣይ ሳምንት ባጋጠሙ ችግሮች፣ክፍተቶች እና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚኖር ጠቁመዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ