የአሽከርካሪዎች ግድያ፣ ዝርፊያና እንግልት እንዲሁም እገታ እየተባባሰ በመምጣቱ አሽከርካሪዎች ስራቸውን ለማቆም ሊገደዱ እንደሚችሉ ስጋት እንዳለው የኢትዮጵያ ከባድ ተሸከርካሪ አሽከርካሪዎች ማህበር ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል።
የከባድ ተሸከርካሪ አሽከርካሪዎች ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ዘውዴ እንደገለፁት በቅርብ ጊዜያት በአሽከርካሪዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረዋል ብለዋል።
መንግስት ችግሩን ለመቆጣጠር ትኩረት እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም እስካሁን ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት እንዳልቻሉ ያነሳሉ። አሽከርካሪዎች ለደህንነታቸው ዋስትና ካልተረጋገጠ ስራቸውን ለማቆም እንደሚገደዱ የጠቀሱ ሲሆን ሁኔታው በሀገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል አብራርተዋል።
ሁኔታው የሃገር ሃብት ላይ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑን የሚገልጹት ስራ አስኪያጁ ፤የሚደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑ በተጨማሪም በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ችግሩ እየጨመረና አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ችግሩ ትኩረት እንደተነፈገዉ ማሳያ ነዉ ብለዋል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ ለመከላከያ ሚኒስቴር፣ ለፌደራል ፖሊስ ፣ ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እንዲሁም ለክልሎች ከሳምንት በፊት በደብዳቤ ያለውን ችግሮች እና ቅሬታቸውን ማሳወቃቸውን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ለጊዜው መፍትሔ ቢሰጡም በወረዳና ቀበሌ ደረጃ ያሉ አስፈጻሚዎች ከአስተዳደር አካላት ጋር በቅንጅት አለመስራታቸው ችግሩን በዘላቂነት ሊፈታው አለመቻሉን የከባድ ተሸከርካሪ አሽከርካሪዎች ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ዘውዴ ተናግረዋል።
የፌደራል መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት በአሽከርካሪዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከልና ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት በተለይም በወረዳና ቀበሌ ደረጃ ያሉ አስፈጻሚዎች ከከፍተኛ አመራሮች ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ጠይቀዋል ።
ምላሽ ይስጡ