👉ወንጀለኛው በ2 ዓመት ከ3 ወር እስራት እንዲቀጣ የተወሰነበት መሆኑን የየካ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል
ሸጋው አየነው የተባለው ተከሳሽ የወንጀል ድርጊቱን ፈጽሞ ሊያመልጥ ሲል በቁጥጥር ስር የዋለው የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ/ም በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ማራቶን ህንፃ ተብሎ ከሚጠራው ስፍራ ነው።
በዕለቱ ወንጀል ፈጻሚው የግል ተበዳይ ከትራንስፖርት ሲወርድ ጠብቆ ከኪሱ የነበረውን ሳምሰንግ A14 ሞባይል ሰርቆ በአካባቢው በነበረ የቆሻሻ መውረጃ ትቦ ውስጥ ገብቶ ሊሰወር እንደሞከረ የየካ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ገልጿል።
ተከሳሽ ምንም እንኳ ለማምለጥ ሙከራ ቢያደርግም መደበኛ የክትትል ስራቸውን እየሰሩ የነበሩ የስውር ክትትልና ኦፕሬሽን ቡድን አባላት ከገባበት የቆሻሻ መውረጃ ትቦ ተከታትለው በመግባት ከነ ኤግዚቢቱ ሊይዙት መቻላቸውን የወንጀል ምርመራ መዝገቡ ያስረዳል። ተከሳሹም ተይዞ ወደ ፖሊስ መምሪያው ከተወሰደ በኋላ መዝገብ በማደራጀት በአቃቤ ህግ ክስ ሊመሠረትበትም ችሏል።
ጉዳዩን በፈጣን ችሎት የተመለከተው በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የካ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ/ም በዋለው ችሎት ተከሳሽን ያርማል ሌሎች ወንጀል ፈጻሚዎችን ያስተምራል ሲል ተከሳሽ ሸጋው አየነው በ2 ዓመት ከ3 ወር እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል።
እንደዚህ ዓይነት የቅሚያ ወንጀል ፈጽመው ለመሰወር የሚሞክሩ ወንጀል ፈጻሚዎች ህጋዊ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው አውቀው ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው እና ህብረተሰቡም ወንጀል ፈጻሚዎችን በማጋለጥ ለፖሊስ የሚያደርገውን ትብብር ማጠናከር እንዳለበት የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል።
ምላሽ ይስጡ