የተበላሹ አውቶብሶችን ጠግኖ ወደ አገልግሎት ለማስገባት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በተፈለገው መጠን መስራት እንዳልተቻለ የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል።
ባለፉት 6 ወራት ውስጥ በአማካይ 157 ያህል አውቶብሶች ተጠግነው ወደ አገልግሎት መግባታቸውን በመግለጽ አሁን ላይ በየቀኑ ጥገና እየተደረገላቸው ወደ ስራ የሚገቡ አውቶብሶች በመኖራቸው ቁጥሩ በየጊዜው ሊጨምር ይችላል ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት የቴክኒክ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ታምሩ ፉፋ ናቸው።
የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማሳለጥ በውስን ስፍራዎች የ24 ሰአት አገልግሎት መስጠት እንደተጀመረ አስታውሰው፤ በብልሽትና በተለያዩ ምክንያቶች ከ15 አመታት በላይ ለሆነ ጊዜ አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ባሶችን ጠግኖ ወደ ስራ የማስገባት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ከውጭ የሚመጣ የመለዋወጫ እቃ ግብዓት የማይፈልጉ አውቶብሶችን በፍጥነት በመጠገን ወደ ስራ እንዲገቡ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ለስራው በጀት እየመደበ ቢሆንም፤ በአገልግሎት አሰጣጥ ሒደት የነዳጅ እጥረት ተግዳሮት መፍጠሩ እንዳለ ሆኖ፤ ለጥገና ስራውም የመለዋወጫ እቃ እንደ ልብ አለመገኘቱ ሌላው ተግዳሮት ነው ብለዋል፡፡
ፈጽሞ ሊጠገኑ የማይችሉና ሊወገዱ የሚገባቸው ውስን አውቶብሶች መለየታቸውን ያስታወቁት ኃላፊው፤ እነርሱን ለማስወገድ የበላይ አመራር ውሳኔ እየተጠበቀ ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት አዳዲስ አውቶብሶችን ገዝቶ ወደ ስራ ከማስገባት ባሻገር፤ ጥገና የሚያስፈልጋቸውን ጠግኖ ለአገልግሎት እያበቃ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ