👉ሙሉ መልዕክታቸው እንደሚከተለው ቀርቧል
ለ29ኛው የዐድዋ ድል በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ።
ዐድዋ ለሰላም የተደረገ ዘመቻ ነው። ከዐድዋ ዘመቻ በፊት ኢትዮጵያውያን ለሰላም ያላቸውን የጸና አቋም ደጋግመው ገልጸዋል። ለሰላም ያላቸው አቋም የጠላት ፉከራዎችንና ትንኮሳዎችን በትዕግሥት አስከማለፍ የደረሰ ነበር።
እንደሚታወሰው የወራሪው የኢጣልያ ጦር ባንዳ ይመለምል ነበር። ባንዳ ያስታጥቅ ነበር። የባንዳ ተላላኪዎችን በመንግሥት ውስጥ ለማሥረግ ይሞከር ነበር። ሽብር ይነዛ ነበር። የኢትዮጵያን መንግሥት ይከስ ነበር። አንዳንድ ቦታዎችን ለመያዝ ይሞክር ነበር። በዓለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያን ለማሳካት ይፍጨረጨር ነበር። ኢትዮጵያ ይሄንን ሁሉ በትዕግሥት እና በዝግጅት ትመለከተው ነበር።
ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ በጦርነት ኖረዋል። በዚህ የተነሣ የጦርነትን አስከፊ ገጽታ ያውቁታል። ስለሚያውቁትም በቻሉት አማራጭ ሁሉ ይሸሹታል። ለሰላማዊ አማራጭ አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋሉ። አንዳንድ ጊዜም ለሰላም ሲሉ ከአስፈላጊው በላይም ያደርጋሉ። ይሄንን ሁሉ ገፍቶ የሚመጣ ጠላት ሲገጥማቸው ግን ለሰላም ሲሉ ዘምተው፤ ለሰላም ሲሉ ያሸንፋሉ።
የዐድዋ ዘመቻም እንደዚሁ ነው። የወራሪው የኢጣልያ ጦር ወደ ጦርነት እንዳይገባ ተለምኗል። የሰላም አማራጮች ቀርበውለታል። ኩራትና ትዕቢት የሞሉት አናት፤ ሰይፍና ጎራዴ የመቱት አንገት እንደሚሉት ሆነ። የኢትዮጵያን ትዕግሥት እንደ ፍርሃት፤ የኢትዮጵያን የሰላም መንገድ እንደ ሽንፈት ቆጠረው።
ጠላቶቻችን ምንጊዜም የስሌት ስሕተት ይሠራሉ። ትኅትናችን፣ ትዕግሥታችንና ሰላም ወዳድነታችን ያሳስታቸዋል። ወራሪው የኢጣልያ ጦርም ተሳሳተ ኢትዮጵያውያን ግን እየታገሡ ይዘጋጁ ነበሩ። በሁሉም ረገድ ሰላማቸውን ለመጠበቅ ዝግጁ ነበሩ። ነጻነት ፣ ሉዓላዊነት እና ከብር የሚገኘት የሀገር ሰላምን በመጠበቅ መሆኑን ያውቃሉ። ስለዚህ ሰላማቸውን በክንዳቸው ለመጠበቅ ተዘጋጁ።
የዐድዋ ጦርነት ለሰላምና ለጦርነት በሚዋጉ ኃይሎች መካከል የተደረገ ጦርነት ነው። የአሸናፊነታችን አንዱ ምሥጢርም ይሄው ነው፡፡ ከጦርነቱ በኋላ ወደ በቀልና ጥላቻ እንዳናመራ ያደረገንም ይሄው ነው። ለሰላም ስንል እንጂ ለጦርነት ስንል አልተዋጋንምና።
የዐድዋ ድል ለሰው ልጅ ሉላዊ ዕሴቶች ያለንን ዋጋ አሳይተንበታል። በምርኮኛ እያያዛችን፣ ከተዋጉን ጋር መልሰን ለሰላማዊ ውይይት በመቀመጣችን፣ ለዘላቂ ሰላም በመሥራታችን።
እናቶቻችንንና አባቶቻችንን በድል አድራጊነታቸው ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ ዕሴቶች በከፈሉት ዋጋ ጭምር እናመሰግናቸዋለን። የተዋጉት ለሰላም ሲሉ ነው የተዋጉት ሰላምን እና ሰላማዊ መንገድን እምቢ ካለ ኃይል ጋር ነው።
የዐድዋ ዘማቾች ልጆች ነን። ለሰላም ቅድሚያ እንሰጣለን። ዛሬም ጠላቶቻችን ከተሳሳተ ስሌት እንዳልወጡ እናውቃለን። በሰላማዊ መንገድ የሚመጡትን መቀበል ከዐድዋ ዘማቾች ተምረናል። በሰላም የማይመጡትንም መቅጣት ከዐድዋ ዘማቾች አይተናል። እኛም እንደቀደምቶቻችን የሰላሙን መንገድ እንመርጣለን። ነገር ግን እንደ ቀደምቶቻችን ሁሉ፣ ለሁለቱም ምንጊዜም ዝግጁዎች ነን። የዐድዋ ዘማቾች ልጆች ነንና።
መልካም በዓል ይሁን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርከ
የካቲት 22፣ 2017 ዓ.ም
ምላሽ ይስጡ