የካቲት 22 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)ታሪክን በሙዚቃ፣ በስዕል፣ በተውኔት እና በሌሎች ኪነጥበባዊ ስራዎች የመግለጽ እድል ቢኖርም ኢትዮጵያ ታሪካዊ ሁነቶቿን በተገቢው መልኩ እንዳልተገለጹ ይነገራል፡፡
የአፍሪካዉያን ኩራትና የድል በዓል የሆነዉን የአድዋ ድል በዓል በተለያዩ የኪነ ጥበብ ስራዎች በተለይም በሙዚቃ ተገልጿል፡፡
የአድዋ ድል በዓል ከኪነ ጥበብ ዘርፍ አንዱ በሆነው በስነ ስዕል በተገቢው መልኩ እንዳልተገለጸ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ እንደሚገልጹት ኢትዮጵያውያን አሁን ላለንበት ማንነትና ኩራት የአድዋ ድል ድርሻ ከፍተኛና ዋነኛው ነዉ ይላሉ፡፡
እስካሁን በሙዚቃ ብቻ እንደተገለጸ አንስተው በስነ ስዕሉ ዘርፍ ግን ገና እንዳልተሰራበት ጠቁመዋል፡፡ ስዕል ነገሮችን የመግለጽና የማሳመን ትልቅ ሃይል አለው ብለው የአድዋ ድልን መግለጽ ላይ ግን ገና ጅምር ላይ ያለ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ትውልዱ ላይ ታሪኩን እንዲያውቅ እንዲረዳ ከትምህርት ቤት ጀምሮ ማስተማር ማሳወቅ አለብን በማለት ገልጸዋል፡፡
በተለይም ታሪኮችን ስናስተምርና ስንመዘግብ ከፖለቲካ አውድ ነጻ አድርገን መሆን አለበት ብለው ትውልዱ ንጹህ ታሪክን መዝግቦ በስዕል ለመግለጽና ለመከተብ መነሳሳትን ይፈጥርለታል ብለዋል፡፡
ከላይ የተነሳዉን ሃሳብ የሚያጠናክሩት ሰዓሊና የአለም ስነ ጥበብ ማዕከል መስራችና ባለቤት ሰዓሊ አለም ጌታቸው አድዋ በታሪክ ቅብብሎሽ ውስጥ ትልቅ አበርክቶ እንደነበረዉ ገልጸው ነገር ግን ኢትዮጵያ አለኝ ከምትላቸው ታሪኮቿ መካከል ዋነኛ የሆነዉን አድዋን በስዕል በአግባቡ አልገለጸችዉም በማለት አስረድተዋል፡፡
አክለዉም ሰዓሊ አለም ሰዓልያን ትልቅ ሃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ አጽንዖት ሰጥተው ሊሰሩበት ይገባል ብለዋል፡፡
129ኛው የአድዋ ድል በዓል በነገው እለት በድምቀት ይከበራል፡፡
ምላሽ ይስጡ