አድዋ ከፍተኛ የሃገር ፍቅር ስሜት የታየበት የመላው ጥቁር ህዝቦች ድል መሆኑ ይታወቃል።
በአድዋ ጦርነት የታየው የአሸናፊነት እና የይቻላል እሳቤ ትልቅ ትሩፋት መሆኑን የሚገልጹት የስነ ልቦና ባለሙያው አቶ ልዑል አብርሃም ናቸው።
ባለሙያው የቴክኖሎጂ መስፋፋት ባልነበረበት ወቅት የነጻነትና የማንነት ዋጋን በመረዳት በአሸናፊነት መንፈስ የአድዋን ጦርነት ማሸነፍ መቻሉ እንደማህበረሰብ ጠንካራ እና በሳል ስነ ልቦና እንዲሁም እሳቤ እንደነበረ የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም አሁን ላይ ያለው ትውልድ ልዩነትን በማጥበብ እንደሃገር የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የአሸናፊነት ስነልቦናን ከአድዋ ድል በመውሰድ በተሰማራበት የስራ እንቅስቃሴ የራሱን አድዋ መፍጠር እንደሚገባው ተናግረዋል።
ከድል ታሪኮች መማር ለአንድ ሃገር የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የሚናገሩት የታሪክ ባለሙያው አቶ በላይ ስጦታው የአድዋ ድል ኢትዮጵያ ካሏት ደማቅ ታሪኮች መካከል በቀዳሚነት የሚነሳ መሆኑን ነው የሚናገሩት።
ከድሉ የተገኙ ልምዶችን በመቅሰም የአንድነትና የይቻላልን ስነ ልቦና ለመገንባት ድሉን የሚዘክሩ ተግባራትን ማከናወን እንዲሁም አሁን ላይ በትውልዱ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም የሚያስችሉ ስራዎችን በማከናወን በዓሉን ማክበር እና ደማቅ ታሪክን ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።
አድዋ ለሃገር ነጻነት እና ልዕልና የተከፈለ የደም ዋጋ መሆኑን በመረዳት የቀደምት አባቶችን ልምድ መውሰድ እና የዘመኑን አድዋ መፍጠር እንደሚገባ ተመላክቷል።
ምላሽ ይስጡ