የአድዋ ድል ታሪክ በማዕከል ደረጃ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎችና በኢትዮጵያዊያን አንደበት የሚዘከር መግባቢያ ቋንቋ ነው ሲሉ መናኸሪያ ሬዲዮ ያነጋገራቸው የቤንሻንጉል ጉምዝ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትጵያ እና የጋምቤላ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች ገለጹ፡፡
የአድዋን የድል ታሪክ እና ሚስጢር በሚያስታውሱ እና በሚያስተምሩ፣ መርሃ ግብሮች፣ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በዓሉ እንደሚከበር የገለጹት የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ አርገታ፣ የአድዋ ጀግኖች የልጅ ልጆቻቸው በየመድረኩ ተገኝተው ከአባቶቻቸው የሰሙትን የድል ሚስጢር ለዛሬው ትውልድ ይተርካሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በየዓመቱ በዓሉን ከማክበር ባሻገር፣ የአድዋ ጀግኖች ለአገራቸው ነፃነት እንደታገሉ ሁሉ የዛሬው ትውልድም ሀገሪቱ የሚገጥሟትን የውስጥና የውጭ ችግሮች ለማሸነፍ፣ በጋራ መቆም አለባቸው ሲሉም አቶ ሀብታሙ አክለዋል፡፡
የአድዋ ድል በዓል በክልሉ በሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች ዘንድ ለማክበር ዝግጅት መደረጉን የገለጹት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ፣ አድዋ ከምንም በላይ ኢትዮጵያዊያን የምንግባባበትና አንድ የሚያደርገን የጋራ አሻራችን ነው ብለዋል፡፡
አክለውም አባቶቻችን በአድዋ እንዳሸነፉት ሁሉ የዛሬው ትውልድም በተሰማራበት መስክ ሁሉ ጠንክሮ በመስራት የኢትጵያን አሸናፊነት በድጋሚ ለማረጋገጥ ድህነትን ድል በመንሳት ዘመናዊውን አድዋን ለማሳየት ቁርጠኛ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡፡
በአንዳንድ ክልሎች የአድዋ በዓል አከባበር እና ስለ ድሉ ያለው ግንዛቤ አሁንም ድረስ ዝቅተኛ መሆኑን የሚያነሱት የጋምቤላ ክልል የባህል ታሪክ ቅርስ ጥናት እና ልማት ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ በፍቃዱ ናቸው፡፡
በዚህም አድዋ በክልሉ ህዝብ ዘንድ በትልቁ እንዲሳል ቢሮው በድሉ ዙሪያ ትምህርታዊ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮችን፣ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በማካሄድና ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በመተባበር የአድዋን ታሪክ እና ፋይዳ የሚያንጸባራቁ ፕሮግራሞችን ለማቅረብ፣ ሰፋፊ ስራዎችን ለመስራት መታቀዱን ተናግረዋል።
የአድዋ ድል የኢትዮጵያውያን አንድነት፣ ጀግንነት እና ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር የሚያሳይ ታላቅ ድል ነውና ይህን ታሪክ ለትውልድ ማስተላለፍ የሁሉም ኃላፊነት እንደሆነም አመላክተዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ