ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል አገራት ልማት ባንክ (New Development Bank) አባል ለመሆን በይፋ ጥያቄ ማቅረቧ ተገልጿል። ጥያቄው ተቀባይነት ካገኘ ኢትዮጵያ ለተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች በተለይም ለመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ ለኃይል፣ ለውሃ አቅርቦት እና ለትራንስፖርት ዘርፎች ዝቅተኛ የወለድ መጠን ያለው ብድር እንድታገኝ የሚያስችላት አማራጭ እንደሚሆን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ለመናኸሪያ ሬዲዮ ገልጸዋል።
የብሪክስ ባንክ አባል መሆን በምዕራባውያን አገራትና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ላይ ያለውን ጥገኝነት በመቀነስ አማራጭ የገንዘብ ምንጭ እንደሚሆን የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ እዮብ አዳሙ ተናግረዋል።
ባንኩ ለአባል አገራቱ ፕሮጀክቶችን ለመንደፍ እና ለመተግበር እንዲሁም አቅምን ለማጎልበት የቴክኒክ ድጋፍ ስለሚያደርግ ኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክቶቿን በብቃት እንድትወጣ ያግዛታል ብለዋል።
በብሪክስ ባንክ ውስጥ መሳተፍ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ያላትን ድምጽ ከፍ ከማድረጉም በተጨማሪ፤ ከሌሎች የብሪክስ አባል አገራት ጋር የንግድና የፖለቲካ ትስስር እንድትፈጥር እድል ይፈጥርላታል ያሉት ደግሞ ሌላኛው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ ናቸው።
የብሪክስ ባንክ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች በጨረታዎች ላይ የመሳተፍ እና ተጠቃሚ የመሆን ዕድል እንደሚፈጥርላቸው አስታውቀዋል፡፡
ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለኢኮኖሚው ዕድገት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለውም ነው ያብራሩት።
የብሪክስ ባንክ አባል መሆን የሚኖሩትን ጥቅሞች ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለማጣጣም ብድርን በአግባቡ ማስተዳደር፣ ፕሮጀክቶችን በወቅቱ ማጠናቀቅ እና ከአባልነት ጋር ተያይዘው የሚመጡትን ግዴታዎች መወጣት እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎቹ ጠቁመዋል።
ምላሽ ይስጡ