በጋምቤላ ክልል ህጻናትን በቤት እንስሳት የመለዋወጡ ልማድ አሁንም ድረስ አለመቀረፉ እንዳሳሰበው የገለጸው የክልሉ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ነው፡፡
ቢሮው አሁንም ድረስ በታጣቂዎች የሚፈጸውን ህገ-ወጥ የህጻናት ዝውውር መቆጣጠር አለመቻሉ ችግሩን አባብሶታል ብሏል፡፡
የቢሮው ሃላፊ ካሪያት ኦጅሉ አሁንም ድረስ ድንበር ተሻግረው ወደ ክልሉ በሚገቡ እና በክልሉ ባሉ ታጣቂ ሃይሎች አዳጊ ህጻናት በህገወጥ መልኩ እየተዘዋወሩ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚዳረጉ አረጋግጠዋል፡፡
ህጻናቱ ከደቡብ ሱዳን በሚመጡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች እየተሰረቁ መሆኑን ገልጸው፤ በተለያዩ ጊዜያት በህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ከደቡብ ሱዳን ጋር ውይይት እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
ከስርቆት ባለፈ አብዛኛውን ጊዜ ህጻናትን በቤት እንስሳት የመለዋወጥ ልማድ እንደሚስተዋል የተናገሩት ኃላፊዋ፤ መፍትሄ ለማበጀት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ታጣቂዎች የህጻናት ዘረፋ በሚፈጽሙባቸው ቦታዎች የሚኖሩ ዜጎች በስጋት ምክንያት በስፍራው ተረጋግተው መኖር እንዳልቻሉ ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቀዋል፡፡
እስካሁን ድርጊቱን መቆጣጠር ባለመቻሉ ለክልሉ አሳሳቢ እንደሆነበት ተናግረዋል፡፡
የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መላኩ ባዬ ችግሩ በተደጋጋሚ እንደሚከሰት አምነው፤ ጉዳዩን ለመፍታት በክልሉ ካሉ የፍትህ አካላት እና ታጣቂዎች ጋር ንግግር እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያመላከቱት፡፡
ሕገ-ወጥ የሕጻናት ዝውውርን ለመግታት የቁጥጥር ስርዓቱን ማጠናከር እና በተቀናጀ መልኩ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ መስራት እንደሚገባ ተገልጻል፡፡
ምላሽ ይስጡ